ኢትዮጵያ መድን በተከላካዩ ጉዳይ ደብዳቤ አውጥቷል።
ባሳለፍነው ዓመት የዝውውር መስኮቱ አጋማሽ ላይ ከሀዋሳ ከተማ የስድስት ወር ቆይታ በኋላ ኢትዮጵያ መድንን የተቀላቀለው ሚሊዮን ሰለሞን ዘንድሮ ድንቅ የውድድር ዓመት እያሳለፈ ባለበት ሁኔታ ጉዳት አስተናግዶ ከሜዳ ከራቀ መሰነባበቱ ይታወቃል።
ህክምናውን እንዲከታተል ፍቃድ ቢሰጠውም በአሁኑ ሰዓት ሚሊዮን በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኝ መሆኑ ተሰምቷል። ሆኖም የተጫዋቹ ባለቤት ኢትዮጵያ መድን ወደ ሄደበት ሀገር ስለመሄዱ አለማሳወቁን እና ክለቡም ስለ ጉዞው የሚያቀው ነገር እንደሌለ አውቀናል። በዚህም መነሻነት ያለበትን ሁኔታ እንዲያሳውቅ ክለቡ ይፋዊ ደብዳቤ ያወጣ መሆኑን አረጋግጠናል።
በቀጥታም ባይሆን ሚሊዮን ወደ ዩናይትድ ስቴትስ የተጓዘው ህክምናውን ለመከታተል እንደሆነ እና ወደ ሀገር ቤት እንደሚመለስ እየገለፀ እንደሆነ ሲነገር ሰምተናል። በዚህ ጉዳይ ላይ የሚሊዮን ምላሽ ለማግኘት ጥረት እያደረግን ሲሆን እንዳገኘነው የምናሳውቅ ይሆናል። እንዲሁም በቀጣይ የክለቡ ውሳኔ ምን ይሆናል የሚለውን ተከታትለን የምናቀርብ ይሆናል።
የኋላ ደጀኑ ሚሊዮን ሰለሞን ከዚህ ቀድሞ በአዲስ አበባ፣ ሲዳማ ቡና እና አዳማ ከተማ እና ሀዋሳ ከተማ ተጫውቶ ማሳለፉ ይታወቃል።