28ኛው ሳምንት በአንድ ደረጃና በስድስት ነጥቦች ልዩነት የተቀመጡት ቡድኖች አስፈላጊ ነጥብ ለማግኘት በሚፋለሙበት ጨዋታ አሀዱ ይላል።
ከነገው ተጋጣሚያቸው በስድስት ነጥቦች ርቀው 16ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት አዳማ ከተማዎች በሊጉ ለመቆየት በሚያደርጉት ጥረት ወሳኝ የሆነውን ጨዋታ ነገ ያደርጋሉ።
አዳማ ከተማ በሁለተኛው ዙር ቀዳሚ ጨዋታ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ላይ ድል ካደረገ በኋላ ላለፉት ሰባት መርሐ-ግብሮች ከድል ጋር መራራቁን ተከትሎ ከወራጅ ቀጠናው መውጣት አልቻለም። ቡድኑ ባለፉት ሰባት ጨዋታዎች ሙሉ ነጥብ ካለማግኘቱ በተጨማሪ አራት ሽንፈቶች ማስተናገዱም ከበላዩ ካሉት ቡድኖች በነጥብ እንዲርቅ አድርጎታል።
ቡድኑ በመጨረሻው ጨዋታ ከተከታታይ ሁለት ሽንፈቶች መልስ ነጥብ መጋራት ቢችልም የኋላ እና የፊት መስመሩ ላይ ጉልህ ችግር እንዳለም አስመልክቷል፤ ባለፉት ሦስት መርሐግብሮች ስድስት ግቦች ማስተናገዱ እንዲሁም ሁለት ግቦች ብቻ ማስቆጠሩም የዚህ ማሳያ ነው። ከዚህ መነሻነት እነዚህን የቅርብ ጊዜ ስህተቶች ካላረመ በነገው ጨዋታ ነጥብ ይዞ ለመውጣት ሊቸገር ይችላል። በተለይም እንደአጠቃላይ ያለው የመከላከል መዋቅር ማስተካከል የአሰልጣኝ አብዲ ቡሊ ቀዳሚ ስራ ይሆናል ተብሎ የሚገመት ሲሆን በዋናነት ደግሞ የመልሶ ማጥቃት የማቆም አቅማቸው ከፍ አድርገው መግባት ይኖርባቸዋል።
ከገጠማቸው ተከታታይ ሽንፈት ለማገገም ጨዋታቸውን የሚያከናውኑት መቐለ 70 እንደርታዎች ሀያ ስምንት ነጥቦች በመሰብሰብ በወራጅ ቀጠናው ላይ ይገኛሉ።
በሁለተኛው ዙር ከተከናወኑ ስምንት ጨዋታዎች ስድስት ሽንፈቶች አስተናግዶ በሁለቱ ድል ያደረገው መቐለ 70 እንደርታ በቅርብ ሳምንታት ባስመዘገባቸው ውጤቶች ወደ ወራጅ ቀጠናው ገብቷል። በምዓም አናብስቱ ቤት ከምንም በላይ ክፍተት የሆነው የመከላከል አጀረጃጀቱ ጥንካሬ ከጊዜ ወደ ጊዜ መዳከም ሲሆን የግብ ማስቆጠር ችግሩም የራሱን ድርሻ ይይዛል። ለማሳያም ቡድኑ በሁለተኛው ዙር በተካሄዱ ስምንት ጨዋታዎች በድምሩ 13 ግቦችን ሲያስተናግድ በተቃራኒው 6 ግቦችን ተጋጣሚ ላይ አስቆጥሯል።
በሀዋሳ ከተማ አምስት ግቦች በባህርዳር ከተማ ደግሞ አራት ግቦች አስተናግዶ ሽንፈት ባስተናገደባቸው ጨዋታዎችም ለቡድኑ መዋቅራዊ እና ግለ-ሰባዊ የመከላከል ድክመቶች ማሳያዎች ናቸው። ይህንን ተከትሎ የአሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬ ትልቁ ስራ የመከላከል አደረጃጀቱን ማስተካከል ይሆናል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን በተለይም ግለ-ሰባዊ የመከላከል ስህተቶች መታረም የሚገባቸው ድክመቶች ናቸው።
የሆነው ሆኖ በቀጥተኛ እንዲሁም በፈጣን ሽግግር አጨዋወት ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት የሚያደርገው ቡድኑ ነገም አዳማ ከተማን ለማሸነፍ የሚመርጠው ስልት ይቀይራል ተብሎ ባይገመትም ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች የሚገኙትን ጥቂት ዕድሎች በመፈፀም ረገድ የተስተዋሉበትን ድክመቶች መቅረፍ ይኖርብታል።
ምንም እንኳን በመካከላቸው የስድስት ነጥብ ልዩነት ቢኖርም በደረጃ ሰንጠረዡ የወራጅ ቀጠና ላይ የሚገኙት ቡድኖቹ ሰፊ ስራ በሚጠብቃቸው ቀጣይ መርሐ-ግብሮች ስንቅ የሚሆን ውጤት ለማግኘት የሚያደርጉት ፍልሚያ እንደመሆኑ ጨዋታው ተጠባቂ ነው።
በአዳማ ከተማ በኩል ቢኒያም ዐይተን ከጉዳት በማገገሙ ለነገው ጨዋታ ይደርሳል ተብሎ ሲጠበቅ ሌሎች የቡድን አባላትም ለጨዋታው ዝግጁ መሆናቸው ታውቋል። በመቐለ 70 እንደርታ በኩል ቦና ዓሊ እና ሄኖክ አንጃው በጉዳት ምሕረትአብ ገብረህይወት ደግሞ በህመም ምክንያት አይሰለፉም ከዚህ በተጨማሪ የያሬድ ከበደ እና ዓወት ኪዳነ መሰለፍም አጠራጣሪ ነው። ኢማኑኤል ላርያ ግን ቅጣቱን ጨርሶ ነገ ቡድኑን ያገለግላል።
ቡድኖቹ 5 ጊዜ ተገናኝተው መቐለ 70 እንደርታ 3 ሲያሸንፍ አዳማ ከተማ አንዱን አሸንፎ በቀሪው አቻ ተለያይተዋል። መቐለ 8፣ አዳማ 5 ግቦች አስቆጥረዋል። (የተሰረዘው የ2012 ጨዋታ አልተካተተም)