ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች| ሦስት ክለቦች በሊጉ ያላቸውን ቆይታ ለማስቀጠል የሚፋለሙባቸው ጨዋታዎች !

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች| ሦስት ክለቦች በሊጉ ያላቸውን ቆይታ ለማስቀጠል የሚፋለሙባቸው ጨዋታዎች !

የሊጉ የመጨረሻ ወራጅ ቡድን ማን ይሆን? በቀጣይ ዓመት በሊጉ ለመቆየት በሶስት ስታዲየሞች የሚደረጉትን ፍልሚያዎች የተመለከቱ የቅድመ-ጨዋታ መረጃዎች እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል

በሊጉ የመጨረሻ ሳምንት መርሐ-ግብር ላይ ቀጣዩን ወራጅ የሚለዩ ወሳኝ ጨዋታዎች ዛሬ በተለያዩ ሜዳዎች በተመሳሳይ ሰዓት ይደረጋሉ። እግር ኳስ አፍቃሪያን ሁሉ ዓይናቸውን ወደ አበበ ቢቂላ፣ አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታድየም እና ወንጂ ስታዲየሞች በጣሉበት በዚህ ሰዓት የመውረድ ስጋት ያጠላባቸውን ቡድኖች ዕጣ ፈንታ የሚወስነውን የቅድመ-ጨዋታ መረጃዎች ይዘንላችሁ ቀርበናል።

 

አዳማ ከተማ ከ ሀዋሳ ከተማ

በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ከቀኑ 9:00 ጀምሮ ከሚደረጉት የዕለቱ ወሳኝ ጨዋታዎች አንዱ በሆነው በዚህ ፍልሚያ አዳማ ከተማ በአሁኑ ወቅት በ43 ነጥብ 16ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ የህልውናው ማረጋገጫ ወደሆነችው የመጨረሻዋ ሰዓት ተሻግሯል። ቡድኑ ካለፉት አምስት ጨዋታዎች ውስጥ ሦስቱን መሸነፉ እስከ መጨረሻው ሳምንት ለህልውናው እንዲጫወት ቢስገድደውም ዛሬ በሊጉ ለመቆየት የሚጠበቅበት ብቸኛ አማራጭ ሦስት ነጥብ ማሳካት ብቻ ነው። በመሆኑም ከመጀመሪያው ደቂቃ ጀምሮ የፊት መስመር ጥቃቱን እጅግ በመጫን እና ፈጣን ጎል ለማግኘት በሚጥር ፍጹም አስገዳጅ በሆነ የማጥቃት ታክቲክ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይታመናል። ቡድኑ በተለይም በክንፍ መስመሮች ላይ ፈጣን ሽግግሮችን በመፍጠር የተጋጣሚን ሳጥን ለማጨናነቅ እንደሚሞክር ሲጠበቅ ይህ የመጨረሻ ዕድሉ በመሆኑ ተጫዋቾቹ ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍተኛ ተነሳሽነትና ትኩረት ይዘው መግባት ይኖርባቸዋል።

በአንጻሩ ተጋጣሚው ሀዋሳ ከተማ በ50 ነጥብ 8ኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ ምንም ዓይነት የመውረድ ስጋት የሌለበትና ሙሉ በሙሉ የተረጋጋ ስብስብ ነው። ቡድኑ ካለፉት ጨዋታዎች ከተመዘገቡበት ተለዋዋጭ ውጤቶች ማግስት ዛሬ ያለምንም ጫና የሚጫወት በመሆኑ በሜዳ ላይ ነጻ የሆነ የኳስ ቁጥጥር ብልጫን በመውሰድና ፈጣን የክንፍ ሽግግሮችን በመጠቀም የአዳማን የተጋለጠ የኋላ ክፍል ለመፈተን እንደሚጫወት ይገመታል። ሀዋሳዎች በመሃል ሜዳ ላይ ኳስን መስርተው በመጠጋጋት ወደ ፊት ለመግፋት የሚመርጡ በመሆኑፕኣ ጨዋታውን በራሳቸው የፍጥነት ልክ የመቆጣጠር ዕድላቸው ሰፊ ነው።

 

ወልዋሎ ዓ/ዩ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

ቢጫ ለባሾቹ በ45 ነጥብ 15ኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ ከወራጅ ቀጠናው አፋፍ ጥቂት እርምጃዎች ርቀው ይገኛሉ። ይሁን እንጂ የዛሬው ተጋጣሚያቸው ክብደት የሊጉን ማጠናቀቂያ ዕጣ ፈንታቸውን እጅግ አጣብቂኝ ውስጥ የሚከት ነው። ቡድኑ ባለፈው ሳምንት አርባ ምንጭ ከተማን በማሸነፍ ያገኘውን መነቃቃት ተጠቅሞ የፊት መስመሩን ማሻሻል እንዲሁም የፈረሰኞቹን የአጥቂ ክፍል መግታት የተከላካይ ጥምረቱን ከመቼውም ጊዜ በላይ ንቁ ማድረግ ይጠበቅበታል።

ይህ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ከቀኑ 9:00 ጀምሮ የሚካሄደው ፍልሚያ ለቢጫዎቹ ትልቅ ታሪክ ነው፤ ምክንያቱም ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፍ የሚችል ከሆነ አለመውረዱን በራሱ ጊዜ የሚወስን ሲሆን ሽንፈት የሚያስተናግድ ከሆነ ግን የሌሎችን ቡድኖች ውጤት ለመጠበቅ ይገደዳል።

ፈረሰኞቹ በበኩላቸው በ53 ነጥብ 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠው የውድድር ዓመቱን እያጠናቀቁ ይገኛሉ። ቡድኑ ያለ ምንም የደረጃ ስጋት ወደ ሜዳ የሚገባ ቢሆንም ባለፈው ሳምንት ከፋሲል ከነማ ጋር በነበረው ጨዋታ ደጋፊዎች በፈጠሩት መጠነኛ ግጭት ምክንያት የዛሬውን ጨዋታ ያለ ደጋፊ ለማካሄድ ተገዷል። ጊዮርጊሶች ያለ ምንም ጫና ወደ ጨዋታው እንደ መቅረባቸው በተሻለ መንገድ ለማጥቃት ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይገመታል።

 

ሽረ ምድረ ገነት ከ ሸገር ከተማ

ሽረ ምድረ ገነት በ42 ነጥብ በደረጃ ሰንጠረዡ 17ኛ ደረጃ ይዞ የመጨረሻዋ የህልውና ፍልሚያ ላይ ደርሷል። የዛሬው ጨዋታ በቀጣይ ዓመት በሊጉ ለመቆየት የሚያስችለው ብቸኛው በር በመሆኑ ቡድኑ ሸገር ከተማን ማሸነፍ እና ከዚያም ባሻገር የወልዋሎን እንዲሁም የአዳማ ከተማን ነጥብ መጣል መጠበቅ ግድ ይለዋል። ከተከታታይ አምስት ጨዋታዎች ሁለቱን በማሸነፍ መጠነኛ ተስፋ ማግኘት የቻለው ቡድኑ በዛሬውን ጨዋታ ከመጀመሪያው ደቂቃ ጀምሮ ተጋጣሚው ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠር ግድ የሚለው ሲሆን በቅርብ ሳምንታት መጠነኛ መሻሻሎች ያሳየው የአጥቂ መስመራቸውም በያዘው መንገድ እንዲቀጥል የሚያስችሉ ስራዎች መስራት ግድ ይላቸዋል።

ሸገር ከተማ በ47 ነጥብ 1ዐኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ ከማንኛውም የወራጅነት ስጋት ሙሉ በሙሉ ነጻ የሆነ ክለብ ነው። በቅርብ ሳምንት መቻልን 2 ለ ዐ በማሸነፍ በጥሩ መነቃቃት ላይ የሚገኘው ቡድኑ ባለፈው ሳምንት በሊጉ መቆየቱን አረጋግጦ ያለ ምንም ጫና ወደ ሜዳ የሚገባ በመሆኑ ከባለፉት ሳምንታት በተሻለ ክፍት አጨዋወት ይኖረዋል ተብሎ ይገመታል። ይህ በወንጂ ሁለገብ ስታዲየም የሚደረገው ጨዋታ ከሌሎቹ የወራጅ ቀጠና ፍልሚያዎች ጋር በተመሳሳይ ሰዓት ከቀኑ 9፡ዐ0 ሰዓት ጀምሮ የሚከናወን ይሆናል።