ዳግማዊ ሚኒሊክ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ተቀላቀለ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በመጪው መስከረም ወር ለሚያደርጋቸው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታዎች ዝግጅት ይረዳው ዘንድ ከቀናት በፊት ለተጫዋቾች ጥሪ በማድረግ ዛሬ ዝግጅቱን በይፋ መጀመሩ ይታወቃል።
አስቀድመን ባደረስናቹሁ መረጃ መሠረት ከሲዳማ ቡና ጥሪ የተደረገላቸው 6 ተጫዋቾች ለጊዜው ብሔራዊ ቡድኑን እንደማይቀላቀሉ እርግጥ ሲሆን አሁን ደግሞ ባለፉት ዓመታት ከተለያዩ የዋልያዎቹ አሰልጣኞች ጋር ሲሰራ የቆየው የህክምናው ባለሞያው ብሩክ ደበበ በተመሳሳይ ሲዳማ ቡና ባለበት የአህጉራዊ ጨዋታ ዝግጅት ምክንያት ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር እንደማይገኝ ታውቋል።
የፌደሬሽኑ ሜዲካል ዳይሬክተርም በብሩክ ምትክ ከዚህ ቀደም በቅዱስ ጊዮርጊስ የህክምና ባለሙያ ሆኖ ያገለገለው እና ከኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ቡድን ጋር በአፍሪካ ዋንጫ ወደ ሞሮኮ የተጓዘው የህክምና ባለሙያ ዳግማዊ ሚኒሊክ መተካቱን አውቀናል።

