የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ከነገው ጨዋታ በፊት መግለጫ ሰጥተዋል።

የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ከነገው ጨዋታ በፊት መግለጫ ሰጥተዋል።

ግባችን ጨዋታውን ማሸነፍ ነው” ፓትሪክ ቪየራ

ነገ 10 ሰዓት በባህር ዳር ስታዲየም ከሚደረገው የኢትዮጵያ እና ሴኔጋል ጨዋታ አስቀድሞ የተጋባዡ ቡድን አሠልጣኝ ፓትሪክ ቬየራ 10 ሰዓት ላይ በባህር ዳር ስታዲየም ቡድናቸውን ልምምድ ካሰሩ በኋላ በስፍራው ለተገኙ የመገናኛ ብዙሀን አባላት ተከታዩን መግለጫ ሰጥተዋል።

ስለ ነገው ጨዋታ

ለረጅም ጊዜ በሜዳው ያልተጫወተ ቡድን እንደምንገጥም እናውቃለን። ግን በጥሩ ስታዲየም እና የመጫወቻ ሜዳ ነው የምንጫወተው ፤ ይህ ለእኛ ጥሩ ነገር ነው። ይህ ቢሆንም ግን ጨዋታችንን ለማክበድ የሚሞክር ቡድን ነው የምንገጥመው። ለዚህ መፍትሄዎችን መፈለግ አለብን። የግብ እድሎችም መፍጠር እና ግብ ማስቆጠር አለብን።

አድካሚ ጉዞ አድርገው ስለ መምጣታቸው

ከሞዛምቢክ ረጅም ጉዞ አድርገን ነው የመጣነው። ግን ዋናው ነገር ሜዳው ነው። ጉዞዎች አድካሚ ቢሆኑም ሜዳ ላይ የቤት ስራን መስራት ከተቻለ ወሳኝ ነው።

ስለ ነገው ጨዋታ እቅዳቸው

ግባችን ጨዋታውን ማሸነፍ ነው። ሦስት ነጥቡን ይዞ መውጣት ነው እቅዳችን። የተደራጀ ቡድን እንደምንገጥም እናውቃለን። ከሱዳን ጋር የተደረገውን ጨዋታም አይተናል። ቡድኑ ሚዛናዊ እንደሆነ አይተናል። እኛ ግን ውጤት ፈልገን ነው የመጣነው። የኢትዮጵያ ቡድን ጥሩ ቡድን ነው። ለቡድኑም ክብር አለን። ግን ጨዋታው ሲጀምር 0ለ0 ብሎ ነው። ስለዚህ እኛ ሜዳ ላይ እንደምንሻል ማሳየት እንፈልጋለን።

ስለተጫዋቾች የተናጥል ብቃት እና የቡድን አጨዋወት

በቡድኑ ውስጥ በጣም ብቃት ያላቸው ተጫዋቾች አሉ። ግን ብቃት ብቻውን ጨዋታ ለማሸነፍ በቂ አይደለም። ይሄንን ብቃት ለቡድን አጨዋወት ማምጣት አለብን። ስለዚህ እንደ ቡድን መጫወት ያስፈልጋል።

 

* ተጫዋቾችን ወክሎ የተገኘው ማላንድ ሳር በበኩሉ ” እዚህ በመገኘቴ ደስተኛ ነኝ። እኔ ወደፊት ስላለው ነገር ነው ማሰብ የምፈልገው። ያለፈው ነገር አልፏል። ከቡድን አጋሮቼ ጋር በመሆን የተሻለ ነገር መስራት ነው የምፈልገው።” በማለት በመጨረሻ ሀሳቡን ሰጥቷል።