የዋልያዎቹ አምበል ጋቶች ከነገው ወሳኝ ጨዋታ በፊት ምን አለ?

የዋልያዎቹ አምበል ጋቶች ከነገው ወሳኝ ጨዋታ በፊት ምን አለ?

👉 “ዋናው እቅዳችን ለ2027 የአፍሪካ ዋንጫ ማለፍ ነው”

👉 “እንዲሁ ደርሶ ለመመለስ አይደለም የመጣነው”

👉 “ሞዛምቢክን ለማሸነፍ ነው የመጣነው”

ሦስቱ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በሚያዘጋጁት የ2027 የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በምድብ 10 ከሴኔጋል፣ ሞዛምቢክ እና ሱዳን ጋር የተደለደለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የምድብ ሦስተኛ ጨዋታውን ከሞዛምቢክ አቻው ጋር ለማከናወን ወደ ማፑቶ ማቅናቱ ይታወቃል። ከነገው ጨዋታ አስቀድሞ በተዘጋጀ የቅድመ ጨዋታ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የቡድኑ አሠልጣኝ ዩሐንስ ሳህሌ የሰጡትን ሀሳብ አቅርበን የነበረ ሲሆን አሁን ደግሞ የቡድኑ አምበል ጋቶች ፓኖም በስፍራው ለተገኙ የሞዛምቢክ የመገናኛ ብዙሀን የሰጠውን አጠር ያለ መግለጫ ይዘን ቀርበናል።

የቡድኑ አምበል ጋቶች ፓኖም ስለጨዋታው ዝግጅት ሀሳቡን ሲሰጥ “ከዚህ በፊት ከሱዳን እና ከሴኔጋል ጋር ተጫውተናል። ነገ ደግሞ ከሞዛምቢክ ጋር እንጫወታለን። የነገው ጨዋታ ከባድ ጨዋታ ነው። ከሜዳችን ውጪም ነው የምንጫወተው። በተጨማሪም ከምድቡ መሪ ጋር ነው የምንጫወተው። እኛ ነጥብ ለማግኘት እና በውድድሩ ለመቆየት ነው እዚህ የመጣነው። በአጠቃላይ በጥሩ ሁኔታ ለጨዋታው ተዘጋጅተናል።” በማለት ተናግሯል።

ጋቶች ከሞዛምቢክ ቡድን ጋር በተያያዘ ለቀረበለት ጥያቄ “የሞዛምቢክን ጨዋታዎች አይተናል። ጠንካራ ቡድን ነው። ቀላል ጨዋታ እንደማይሆን እናውቃለን። ለጨዋታው ተዘጋጅተናል። እንዳልኩት በውድድሩ ለመቆየት እንፈልጋለን። ለዚህም ነው ነጥብ ለማግኘት እዚህ የመጣነው ፤ እንዲሁ ደርሶ ለመመለስ አይደለም የመጣነው። ሞዛምቢክን ለማሸነፍ ነው የመጣነው።” ካለ በኋላ እንደ ቡድን ዋና እቅዳቸው ለ2027 የአፍሪካ ዋንጫ ማለፍ እንደሆነ አመላክቷል።