“ጨዋታው በጣም አስፈላጊያችን ነው። ነጥብ ለማግኘት እና በውድድሩ ለመቆየት ማድረግ ያለብንን ነገር እናደርጋለን” ዮሐንስ ሳሕሌ

“ጨዋታው በጣም አስፈላጊያችን ነው። ነጥብ ለማግኘት እና በውድድሩ ለመቆየት ማድረግ ያለብንን ነገር እናደርጋለን” ዮሐንስ ሳሕሌ

በነገው ዕለት ወሳኝ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ከሞዛምቢክ ብሔራዊ ቡድን ጋር የሚያከናውነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አለቃ የቅድመ ጨዋታ ጋዜጣዊ መግለጫ ከደቂቃዎች በፊት ሰጥተዋል።

በ2027 የአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ የአህጉሪቱ ብሔራዊ ቡድኖች በምድብ ተከፋፍለው የማጣሪያ ጨዋታዎችን እያከናወኑ የሚገኝ ሲሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም የምድብ ሦስተኛ ጨዋታውን ከሞዛምቢክ አቻው ጋር ለማከናወን ወደ ማፑቶ አቅንቷል። ነገ 10 ሰዓት ከሚደረገው ጨዋታ አስቀድሞ የዋልያዎቹ አለቃ አሠልጣኝ ዩሐንስ ሳህሌ የቅድመ ጨዋታ ጋዜጣዊ መግለጫ ከአንበላቸው ጋቶች ፓኖም ጋር ሰጥተዋል። በቅድሚያም አሠልጣኙ የሰጡትን ሀሳብ እናቀርባለን።

በቅድሚያ ስለዝግጅታቸው እና ስለጨዋታው አስተያየታቸውን የሰጡት አሠልጣኙ “ሞዛምቢክ ስንመጣ 23 ተጫዋቾችን ይዘን ነው ለነገው ጨዋታ የመጣነው። አንድ ተጫዋች ብቻ ለጨዋታው ዝግጁ ነው ወይ የሚለውን እርግጠኛ አይደለንም። ከህክምና ክፍሉ የምናገኘውን ማረጋገጫ አይተን እንወስናለን። ከእርሱ ውጪ ሁሉም ተጫዋቾች ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው። ጨዋታው በጣም አስፈላጊያችን ነው። ነጥብ ለማግኘት እና በውድድሩ ለመቆየት ማረግ ያለብንን ነገር እናረጋለን ፤ እዚህም የተገኘነው ለዚህ ነው።” በማለት ሀሳባቸውን በስፍራው ለተገኙ የሞዛምቢክ የመገናኛ ብዙሀን ሰጥተዋል።

ስለሞዛምቢክ ብሔራዊ ቡድን የተጠየቁት አሠልጣኙ “የሞዛምቢክ ብሔራዊ ቡድን የምድቡ መሪ ናቸው። ነገ ከእኛ ጋር ሲጫወቱ በምን አይነት የጨዋታ መንገድ እንደሚጫወቱ አናውቀውም። እኛ ይሄ ጨዋታ ሁለተኛ ከሜዳችን ውጪ የምናደርገው ጨዋታ ነው። ሞዛምቢክ በሜዳዋ ነው ሶስቱንም ቸዋታ እያደረገች ያለችው ፥ ይህም የተሻለ ጥቅም እንድታገኝ ያደርጋታል። እኛ ግን ቡድኑ ከሴኔጋል ጋርም ሆነ ከሱዳን ጋር ሲጫወት የነበረበትን መንገድ በደንብ አይተናል። በአጠቃላይ ለጨዋታው ተዘጋጅተናል።” ብለዋል።

በመጨረሻ ስለሞዛምቢክ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች የተጠየቁት አሠልጣኙ “የሞዛምቢክ ብሔራዊ ቡድንን ሁለት የምድብ ጨዋታዎች ገምግመናል። በመጀመሪያው የሴኔጋል ጨዋታ ላይ አንዳንድ አደገኛ ተጫዋቾች በስብስቡ እንዳሉ አስተውለናል። በሱዳኑም ጨዋታ ተመሳሳይ ነገር አስተውለናል። እኛ የተጫዋቾችን የግል ብቃት ብቻ ሳይሆን የቡድኑን አጠቃላይ ብቃት ነው የምናየው። ለዚህም እኛ ስራችንን በሚገባ ለመስራት ተዘጋጅተናል።” በማለት መልሰዋል።