👉 “ከሴኔጋል ጋር መጫወትን አንፈራም፤ ሙሉ አቅማችንን አውጥተን እንፋለማለን ! ”
👉 “የባህር ዳር ሜዳ ጥራት አስደምሞኛል፤ በህይወቴ ካየኋቸው ምርጥ ሜዳዎች አንዱ ነው”
👉 “ጎል ማስቆጠር የአጥቂው የግል ስራ እንጂ አሰልጣኝ የሚያስተምረው ነገር አይደለም”
👉 “ሁለት ቁልፍ ተጫዋቾቻችን ቢጎድሉም የተቀሩት 21 ልጆች ግን ሙሉ በሙሉ ዝግጁ ናቸው”

በ2027 በሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በምድብ ‘J’ ተደልድሎ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በነገው ዕለት በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን ጋር የሚያደርገውን የምድብ ሁለተኛ ማጣሪያ ጨዋታ አስመልክቶ የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ከጨዋታው በፊት በነበረው ይፋዊ የቅድመ ጨዋታ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ከተለያዩ የሜዲያ አካላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሰጡትን ማብራሪያ እንደሚከተለው አቅርበናል።
“ለነገው ጨዋታ ያደረግነውን ዝግጅት አጠናቅቀናል። በሁለት ቢጫ ካርድ ከጨዋታው ውጪ የሆነው መስፍን ታፈሰ እና በጉዳት ምክንያት የማይሰለፈው በረከት ወልዴ በነገው ስብስብ ውስጥ የሉም፤ ከእነሱ ውጪ ያሉት 21 ተጫዋቾቻችን ግን ለጨዋታው ሙሉ በሙሉ ዝግጁ ናቸው። በተጨማሪም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ያዘጋጀው የባህር ዳር ስታዲየም የጨዋታ ሜዳ በኢትዮጵያ ውስጥ ካየኋቸው ምርጥ ሜዳዎች አንዱ በመሆኑ ሁለቱም ቡድኖች በጥሩ ሜዳ ላይ ጥሩ እግር ኳስ እንደሚያሳዩ እምነቴ ነው።”
“ከባለፈው የሱዳን ጨዋታ ጋር ተያይዞ የተነሱትን የግብ እድል አለመጠቀም ስህተቶች በተመለከተ ይሄ ያለፈ ነገር ነው። በእግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ትልልቅ አጥቂዎች እንኳ ለረጅም ጊዜያት ግብ ሳያስመዘግቡ የቆዩበት አጋጣሚ አለ። እኛ የምንችለውን ያህል ቡድኑ ትኩረት እንዲያደርግ እና የላቀ ስነ-ልቦና እንዲኖረው ሰርተናል። እስከ ተቃራኒ ቡድን ግብ ክልል ድረስ መድረስ ችለናል፤ የቀረው ነገር አጥቂዎች በትኩረት አጋጣሚዎችን መጠቀም ብቻ ነው።”
“ስለ ማጥቃት ነፃነት እና ታክቲክ በተመለከተ፤ በተጫዋቾቻችን ላይ ያሰመርናቸው የሜዳ ዞኖች እና የጨዋታ ድርሻዎች አሉ። ከዛ ውጪ ግን አጥቂዎቻችን ግብ ለማስቆጠር የሚያስችላቸውን ማንኛውንም ነፃነት ሰጥተናቸዋል። ችግሩ የነፃነት ማጣት ሳይሆን አጋጣሚዎችን ወደ ግብ አለመቀየር ብቻ ነበር።”
“የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ደረጃ ትልቅ ስም ያለው እና ጠንካራ ቢሆንም በሜዳችን የምንጫወት እንደመሆናችን መጠን ወደ ኋላ የምንልበት ምንም ምክንያት የለም። ተጫዋቾቼ ያላቸውን ሙሉ አቅም አውጥተው ለመጫወት እና ውጤት ለመያዝ 100% ዝግጁ ናቸው። በ38 ዲግሪ የሱዳን ሙቀት ውስጥ እንኳ ሳይበገሩ የታገሉ ተጫዋቾች አሉኝ ስለዚህ በነገው ጨዋታ አዎንታዊ አስተሳሰብ ይዘን የምንገባ ሲሆን ለ90 ደቂቃ ተዋግተን ውጤቱን የምናይ ይሆናል።”

