ቢጫ ለባሾቹ ከፈረሰኞቹ ጋር ጥብ ተጋርተው በመውጣት ለከርሞ በሊጉ መቆየታቸውን ያረጋገጡበትን ውጤት አስመዝግበዋል

በሊጉ ለመቆየት ወደ ሜዳ የገቡት ቢጫ ለባሾቹ ደረጃቸውን ለማሻሻል ከሚጫወቱት ከፈረሰኞቹ ጋር ያደረጉት ጨዋታ አጀማመሩ ላይ ጊዮርጊሶችን ጫና የፈጠሩበት ሲሆን ግብም ማስቆጠር ችለዋል ፤ ኳስ ይዘው ሳጥን ውስጥ በሚገቡበት ቅፅበት የቢጫ ለባሾቹ ተከላካይ ኪሩቤል ወንድሙ ፀጋ ከድር ላይ በሰራው ጥፋት ፍፁም ቅጣት ምት ተሰጥቷቸው ፍፁም ጥላሁን 12ኛው ደቂቃ ላይ ወደ ግብነት ቀይሮ መሪ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል።
ከግቡ መቆጠር በኋላ የተነቃቁት ቢጫ ለባሾቹ የአቻነት ግብ ፍለጋ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስደው የተጋጣሚያቸውን ግብ ክልል ሲደርሱ ቆይተው 34ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥረዋል። በጥሩ አንድ ለአንድ ቅብብል ሳጥን ውስጥ ሲደርሱ ሰመረ ሀፍታይ ላይ በተሰራው ጥፋት ፍፁም ቅጣት አግኝተው ሀፊዝ ኮንኮኒ አስቆጥሮ አቻ ካደረጋቸው ከደቂቃዎች በኋላ ተጨማሪ ግብ ለማግኘት አደገኛ ሙከራዎችን አድርገዋል። በተለየም ነፃነት ገ/መድህን የቆመ ኳስ አሻምቶ ሀፍዝ ኮንኮኒ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገውና ግብ ጠባቂው እንዴት ጨርፎ ያወጣባቸው ሙከራ መሪነቱን ለመረከብ የተቃረቡበት ሲሆን አጋማሹ በአቻ ውጤት ተጠናቆ ለዕረፍት አቅንተዋል።

አዲስ አበባ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት ተመሳሳይ ሰዓት ላይ የሚደረጉ ጨዋታዎች ግዴታ መቋረጥ ስለነበረባቸው ለአርባ ደቂቃ ያህል ተቋርጦ በቀጠለው በሁለተኛው አጋማሽ ቡድኖቹ ቀዝቀዝ ባለ ጨዋታ እንቅስቃሴ ተመልሰው እምብዛም የግብ ማግባት ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። ጨዋታውም በመጀመሪያ አጋማሽ በተቆጠሩ ሁለት ፍፁም ቅጣት ምት ግቦች ነጥብ በማጋራት የተቋጨ ሲሆን ወልዋሎዎቹም ለከርሞ በሊጉ መቆየታቸውን አረጋግጠዋል።

