ታላቁ አጥቂ ጦሩን ተቀላቅሏል

ታላቁ አጥቂ ጦሩን ተቀላቅሏል


በኢትዮጵያ እግርኳስ ከታዩ ምርጥ አጥቂዎች መካከል አንዱ የሆነው አቡበከር ናስር ዳግም ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ ጦሩን ተቀላቅሏል።

አሠልጣኝ ውበቱ አባተን በመንበሩ የሾመው መቻል የወሳኝ ተጫዋቾቹን ውል አራዝሞ አዳዲስ ተጫዋቾችን ከሀገር ውስጥ እና ከውጪ ወደ ስብስቡ በመቀላቀል በቀጣዩ የውድድር ዓመት በዋንጫ ፉክክሩ ለመገኘት እየተንቀሳቀሰ ክረምቱን ያሳለፈ ሲሆን በዛሬው ዕለት ደግሞ ገና በለጋ እድሜው በኢትዮጵያ እግርኳስ የደመቀ ስም ያለውን አጥቂው አቡበከር ናስር በሁለት ዓመት ውል የግሉ አድርጓል።

በክለብ ደረጃ በሐረር ሲቲ ታዳጊ ቡደን መነሻውን በማድረግ ኢትዮጵያ ቡና በመቀላቀል ድንቅ አጥቂ መሆኑን ያሳየው አቡበከር በ2013 የውድድር ዘመን በ24 ጨዋታዎች 29 ጎሎችን በማስቆጠር በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ታሪክ በአንድ የውድድር ዘመን በርካታ ጎል በማስቆጠር ሪከርድ በመያዝ የኮከቦች ሽልማትን ጠራርጎ በመውሰድ ባለ ታሪክ ተጫዋች መሆኑ ይታወሳል። አቡበከር በማስከተል የፕሮፌሽናል እግርኳስ ህይወቱን ለመምራት የደቡብ አፍሪካውን ሀያል ክለብ ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ከዛም ለሱፐር ስፖርት ዩናይትድ እና ለፕሪቶሪየ ዩኒቨርስቲ ክለቦች ቆይታ ቢያደርግም ጉዳት በታሰበው ልክ አቅሙን አውጥቶ  እንዳይጫወት እንደፈተነው ይታወቃል።

ከክለብ አልፎ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ድንቅ ግልጋሎት የሰጠው አቡበከር ዳግም ወደ ሀገር ውስጥ ተመልሶ በዛሬው ዕለት ለመቻል ለመጫወት ፊርማውን ማኖሩን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።