በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የቅጣት ውሳኔ የተላለፈበትን የሀዋሳ ከተማ ተጫዋች በተመለከተ መደበኛ ፍርድ ቤት እግድ አውጥቷል።
የሊጉ የፋይናንስ አሰራር ተቆጣጣሪ ኮሚቴ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የክለቦች የክፍያ ስርዓት አስተዳደር መመሪያ ቁጥር 1/2016 በአንቀጽ 7 በተሰጠው ኃላፊነት መሰረት በአራት ክለቦች እና በ15 ተጫዋቾች ላይ ባደረገው ምርመራ ክለቦቹ የቅድመ ክፍያ (በሦስተኛ ወገን) መክፈላቸውን እና ተጫዋቾቹ መቀበላቸውን አረጋግጫለው በማለት የቅጣት ውሳኔዎችን በክለቦቹ እና በተጫዋቾቹ ላይ ማስተላለፉ ይታወቃል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ቅጣት የተላለፈባቸው አንዳንድ ተጫዋቾች ጉዳያቸውን ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት እየወሰዱት ሲሆን የሀዋሳ ከተማው ተጫዋች እስራኤል እሸቱ ደግሞ ከሳምንታት በፊት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበርን ከሶ ነበር።
የተጫዋቹን ጉዳይ በጠበቃነት እየተከታተሉ የሚገኙት አቶ ብርሃኑ በጋሻው ለዝግጅት ክፍላችን በላኩት መረጃ መሠረት አክሲዮን ማኅበሩ ተጫዋቹ ላይ ያስተላለፈው ውሳኔ ተከሳሽ አስተያየት ከመልስ ጋር እስኪሰጥ ድረስ ውሳኔው ታግዶ እንዲቆይ የቂርቆስ ምድብ 2ኛ ፍ/ብሄር ትናንት በዋለው ችሎት ውሳኔ አስተላልፏል። አክሲዮን ማኅበሩም የቀረበለትን ክስ (10 ገፅ) በተመለከተ እስከ ግንቦት 13 ምላሽ እንዲያቀርብ የተጠየቀ ሲሆን ምላሹን ለመስማትም ግንቦት 18 ቀጠሮ መያዙን ታውቋል።
