ነገ ድል ማድረግ ከቻለ በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ የሊጉን ዋንጫ የሚያሸንፈው አንጋፋው ኢትዮጵያ መድን በ1994 ካነሳው የጥሎ ማለፍ ዋንጫ ወዲህ ከ23 ዓመታት ጥበቃ በኋላ ዋንጫ ወደ ካዝናው ለመክተት ከሌላው የሸገር ተወካይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ይፋለማል።
በኢትዮጵያ ቡና ከደረሰባቸው ሽንፈት በማገገም ሲዳማ ቡናን አሸንፈው ወደ ነገው ጨዋታ የሚቀርቡት ኢትዮጵያ መድኖች ተከታያቸው ኢትዮጵያ ቡና በአርባ ምንጭ ከተማ ሽንፈት ማስተናገዱን ተከትሎ ነገ ድል ማድረግ የሚችሉ ከሆነ የሊጉን ዋንጫ ማንሳታቸው ያረጋግጣሉ።
በውድድር ዓመቱ ዘለግ ላሉ የጨዋታ ሳምንታት በመሪነቱ የተቀመጠው እና ወሳኝ መርሐ-ግብሮችን እያሸነፈ ከሳምንት ሳምንት ለዋንጫው እየቀረበ የመጣው እንዲሁም በሊጉ በርከት ያሉ ድሎች በማስመዝገብ፤ ብዙ ግቦች በማስቆጠር፤ ጥቂት ግቦች በማስተናገድ እንዲሁም ጥቂት ሽንፈቶች በመቅመስ ቀዳሚ የሆነው የገብረመድህን ኃይሌው ቡድን ዘንድሮ በብዙ መመዘኛዎች የተሟላ ቡድን ነበር። የውድድር ዓመቱ ልፋታቸው በዋንጫ ለማጀ ከጫፍ የደረሱት ኢትዮጵያ መድኖች በመጨረሻው ጨዋታ ያሳዩት ብቃት የኢትዮጵያ ቡናው ሽንፈት የቡድኑን ጉዞ ወደ ኋላ ያልጎተተው መሆኑን ያሳየ ነበር፤ በመጨረሻው ጨዋታ ሲዳማ ቡናን ሦስት ለምንም የረታው ቡድኑ በነገው ጨዋታ ከወትሮ ለየት ባለ ተነሳሽነት ወደ ሜዳ ይቀርባል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን በተለይም በውድድር ዓመቱ በጨዋታ በአማካይ 1.3 ግቦችን እያስቆጠረ የዘለቀው የፊት መስመሩ ለተጋጣሚው ፈተና እንደሚሆን ይጠበቃል። በነገው ዕለት ለአስር ዓመታት በተጫዋችነት ያገለገሉበትን ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያሸንፉ ከሆነ የሊጉን ክብር ማንሳታቸውን የሚያረጋግጡት አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ በ2010 ከጅማ አባጅፋር፣ በ2011 ደግሞ ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር ያሳኩትን ክብር ነገ የሚደግሙ ከሆነ በፕሪምየር ሊጉ ታሪኩ ከሦስት የተለያዩ ክለቦች ጋር ዋንጫ በማንሳት ብቸኛው የሚሆኑት አሰልጣኝ ይሆናሉ።
በአርባ ሦስት ነጥቦች 6ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ደረጃቸውን ለማሻሻል የሚረዳቸውን ድል ለማግኘት መሪው መድንን ይገጥማሉ።
ከሦስት ተከታታይ ሽንፈቶች መልስ ስሑል ሽረን በማሸነፍ ወደ ድል መንገድ የተመለሱት ፈረሰኞቹ በመደዳ ከጣሏቸው ነጥቦች መልስ ጨዋታውን ማሸነፍ ቢችሉም ዕድሎችን የመጠቀም ድክመታቸውን ግን አሁንም እንደቀጠለ ነው። ቡድኑ ከተጋጣሚው በተሻለ ተንቀሳቅሶ በርከት ያሉ ዕድሎች መፍጠር ቢችልም ደካማው የአፈፃፀም ብቃቱ በፈጠራቸው ዕድሎች ልክ ግቦችን እንዳያስቆጥር አድርጎታል። ፈረሰኞቹ በርከት ያሉ ግለ-ሰባዊ የመከላከል ድክመቶች ከተስተዋሉባቸው እና አራት ግቦች ካስተናገዱባቸው ሦስት መርሐ-ግብሮች መልስ መረባቸውን አስከብረው መውጣታቸው በአወንታነቱ የሚጠቀስላቸው ነጥብ ቢሆንም የነገ ተጋጣሚያቸው በሊጉ ጥቂት ግቦች ያስተናገደ እና ባለፉት አራት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ያስተናገደ እንደመሆኑ በቅርብ ሳምንታት የተስተዋሉባቸውን የአፈፃፀም ድክመቶች ማረም ይኖርባቸዋል።
በኢትዮጵያ መድን በኩል አጥቂው አለን ካይዋ በቅጣት ምክንያት አይሰለፍም፤ ከዚህ በተጨማሪም አሁንም መሐመድ አበራ ከጉዳቱ ሙሉ ለሙሉ ባያገግምም የጨዋታ ዕለት ስብስብ አካል እንደሚሆን ይጠበቃል። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል አማኑኤል ኤርቦ በቅጣት ተገኑ ተሾመ እና አማኑኤል ተርፉ በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጭ ሲሆኑ የተቀሩት የቡድኑ አባላት ግን ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው።
ሁለቱ ክለቦች እስካሁን በሊጉ 28 ጊዜ የመገናኘት ታሪክ ሲኖራቸው 19 ጊዜ ያሸነፈው ቅዱስ ጊዮርጊስ 50 ጎሎች ፣ 3 ጊዜ ያሸነፈው መድን ደግሞ 15 ግቦችን አስቆጥረው 6 ጊዜ ነጥብ ተጋርተዋል።