የመውረድ ስጋት ላይ ያሉ ቡድኖችን ያገናኘው የጨዋታ ሳምንቱ ማሳረጊያ መርሐግብር ነጥብ በማጋራት ተጠናቋል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ32ኛው ጨዋታ ሳምንት ወላይታ ድቻን ሲያሸንፉ ይዘው ከገቡት ቋሚ አሰላለፍ የአንድ ተጫዋች ቅያሪ በማድረግ ሽመክት ጉግሳን በፍቃዱ ዓለሙ ተክተው ሲቀርቡ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባሳለፍነው ጨዋታ ሳምንት በድሬዳዋ ከተማ ሲረቱ ይዘው ከገቡት የመጀመሪያ ቋሚ ስብስብ ፓላክ ቾል እና ተስፋዬ ታምራት አሳርፈው በምትካቸው ፍሬው ጌታሁን እና ዩሐንስ ኪዳኔን ይዘው ወደ ሜዳ ገብተዋል።
ሁለቱን በወራጅ ስጋት ላይ ያሉ ቡድኖችን ያገናኘው የጨዋታ ሳምንቱ ማሳረጊያ ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች በመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎች መረጋጋት የተሳናቸውን እንቅስቃሴ ያስመለክቱን እንጂ ከተከላካይ ጀርባ በሚጣሉ ኳሶች ወደ ተጋጣሚዎቻቸው ግብ ክልል መድረስ ችለዋል። ይሁን እንጂ ቡድኖቹ የጠራ የግብ ማግባት ሙከራ ሳያስመለከቱን ጨዋታው ወደ የአጋማሹ አካፋይ ላይ ደርሷል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመጠኑ በኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስደው መጫወት የቻሉ ሲሆን ወደ ፊት ሄደው ጫና በማሳደርም የተሻለ ተንቀሳቅሰዋል፤ 27ኛው ደቂቃ ላይ በጥሩ ቅብብል ገብተው አዲስ ግደይ ከሳጥን ውጭ ጠጠር ያለ ሙከራ አድርጎ ግብ ጠባቂው ኢድሪሱ አብዱላሂ ይያዝበት እንጂ የመጀመሪያ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ሆኖ ተመዝግቧል። እንዲሁም አሸናፊ ጥሩነህ ኳሱን ከራሳቸው ሜዳ ለማራቅ ጥረት ሲያደርግ ኳሱ ተጨርፎ ሳጥን ውስጥ ሱሌይማን ሀሚድ ጋር ደርሶ ብቻውን ሆኖ አግኝቶ መረጋጋት ተስኖት ኳሱን በመጀመሪያ ንክኪ ወደ ግብ መጥቶ ግብ ጠባቂው በቀላሉ የተቆጣጠረበት አጋጣሚ ሌላኛው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወርቃማ እድል የነበረ ቢሆንም ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል።
በመጀመሪያው አጋማሽ እብዛም የግብ ማግባት ሙከራዎችን ባያደርጉም በመልሶ ማጥቃት ጫና ለማሳደር ሲጣጣሩ የነበሩት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች 30ኛው ደቂቃ ላይ በፍቃዱ ዓለሙ አማካኝነት መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ መረብ ላይ ማሳረፍ ቢችሉም የእለቱ ረዳት ዳኛ ሙስጠፋ መኪ ከጨዋታ ውጪ በማለታቸው ግቡ ተሽሮባቸዋል።
ወሳኝ እና ደረጃ ለማሻሻል የሚደረግ ጨዋታ ከመሆኑ አንፃር ቡድኖች ጠንካራ ፉክክር እያደረጉ በመልሶ ማጥቃት እድሎችን ለመፍጠር በፈጣን ሽግግር እንዲሁም መጠነኛ ጥንቃቄ ጥሩ የጨዋታ እንቅስቃሴ ለተመልካች ያስመለክቱ እንጂ ጨዋታው እንደተጠበቀው በሙከራዎች መታጀብ ግን ሳይችል ቀርቷል። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመጀመሪያ አጋማሽ ወደ ሳጥን በመድረስ ረገድ የተሻለ እንቅስቃሴ በአጋማሹ ሲያደርጉ አስተውለናል። አጋማሹም ግብ ሳይቆጠርበት ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል ገብተዋል።
ከመልበሻ ክፍል የተጫዋቾች ቅያሪ ሳያደርጉ የተመለሱት ቡድኖቹ ልክ እንደመጀመሪያው አጋማሽ ኳስ ተቆጣጥረው ረጃጅም ኳሶችን እየጣሉ ወደ ሶስተኛው ሜዳ ክፍል ሲደርሱ ያስተዋልን ቢሆንም ግብ ክልል አከባቢ ሲደርሱ አጨራረስ ላይ ፍፁም ደካማ እንቅስቃሴ አድርገዋል። በጨዋታውም ቡድኖች መልሶ ማጥቃትን ምርጫቸው አድርገው ተጋጣሚ ቡድን ግብ ክልል በተደጋጋሚ ደርሰዋል፤ ሆኖም ግን ይዘው ገብተው ሙከራ ለማድረግ ሲጥሩ ኳሶቹ እየቆረጠባቸው ሲቸገሩ እያስተዋልን ጨዋታው ወደ ስልሳዎቹ ደቂቃዎች ድረስ ዘልቋል።
በሁለተኛው አጋማሽ በአንፃራዊነት ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ በመድረስ የተሻሉ የነበሩትን ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በ66ኛው ደቂቃ ላይ በሀብታሙ ሸዋለም አማካኝነት በቆመ ኳስ ያደረጉት ሙከራ ሲጠቀስ ብዙም ጠንካራ ያልሆነ ኳስ ቀጥታ ወደ ግብ መጥቶ ግብ ጠባቂው ፍሬው ጌታሁን በቀላሉ የተቆጣጠረባቸው ሙከራ ይጠቀስ እንጂ እምብዛም ፈታኝ የሆነ ሙከራ አልነበረም። ይሄኛው ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ይጠቀስ እንጂ ሌሎችም በፈጣን መልሶ ማጥቃት ጥቃቶችን መሰንዘራቸውን እስከመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ድረስ አጠናክረው መቀጠል ችለዋል። ሆኖም ግን የጠራ ሙከራ ሳያስመለክቱን ጨዋታው ወደ መጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች አምርቷል።
ንግድ ባንክ ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃር ሙከራዎችን በማድረግ አኳያ ቀዝቀዝ በተመለሰቡት በሁለተኛው አጋማሽ በ83ኛው ደቂቃ ላይ ሳይመን ፒተር ላይ ያሬድ የማነ በሰራው ጥፋት አደገኛ ቦታ ላይ ቅጣት አግኝተው ወደ ግብነት ይቀይራሉ ተብሎ ሲጠበቅ ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል፤ ቅጣት ምቱን ኤፍሬም ታምራት ቀጥታ ወደ ግብ መጥቶ ከግቡ አግዳሚ ለጥቂት ከፍ ብሎ ያለፈበት ሙከራ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ሶስት ሊያስገኝላቸው የቀረበ አጋጣሚ ነበር።
መደበኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ብቻ ቀርተው እያለ በ89ኛው ደቂቃ ላይ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ወርቃማ እድል አግኝተው አምክነዋል፤ በተጠቀሰው ደቂቃ ላይ አቤል ሀብታሙ በረጁም ከተከላካይ ጀርባ የተጣለ ኳስ ፍጥነቱን ተጠቅሞ ደርሶ ሳጥን ውስጥ ይዞ በመግባት ብቻውን ለነበረው ለኢዮብ ገብረማርያም ያሻገረውን ኳስ ተጫዋቹ ብቻውን ሆኖ ኳሱን ቢያገኝም ሳይጠበቅ ወደ ላይ ያወጣበት አጋጣሚ ለኤሌክትሪኮች ሶስት ነጥብ ለማስገኘት ያለቀ አጋጣሚ ቢሆንም ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል።
በአጠቃላይ በጨዋታው ሁለቱም ቡድኖች ሙሉ ሶስት ነጥብ ይዘው ወጥተው ደረጃቸውን ለማሻሻል ብርቱ ፉክክር ያደረጉ ሲሆን በተደጋጋሚ በመልሶ ማጥቃት ከሳጥን ሳጥን እየደረሱ እንቅስቃሴዎቹን ወደ ግብ መቀየር ተስኗቸው ጨዋታው ጥራት ያላቸው የግብ ሙከራዎች እንዲሁም ግብ ሳይቆጠርበት ነጥብ በማጋራት ተጠናቋል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ አስተያየታቸውን የሰጡት አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ’ በሁለቱም አጋማሾች የተሻለ ስለመንቀሳቀሳቸው አንስተው ከፊታችን ላሉ ጨዋታዎች ትኩረት አድርገው የተሻለ ነገር ለማድረግ እንደሚጥሩ ገልፀዋል።አሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ በበኩላቸው አልመው የገቡት ሶስት ነጥብና ሶስት ነጥብን እንደነበር አንስተው በቀጣይ ጨዋታዎችም ከሜዳ ውጭ ያሉ ነገሮች እንደሚያሳስባቸውም እንዲሁ ገልፀዋል።