ከያዝነው ወር የመጨረሻዎቹ ቀናት አንስቶ በሦስት ሀገራት ለሚደረገው የቻን የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ ሁለት ኢትዮጵያዊያን ዳኞች ሀገራችንን እንደሚወክሉ ተረጋግጧል።
ሦስቱ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የሆኑት ታንዛኒያ ፣ ዩጋንዳ እና ኬኒያ በጣምራ በመሆን የ2025 የቻን የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎችን ያስተናግዳሉ። ከሐምሌ 26 አንስቶ ለሰላሳ ሁለት ቀናቶች በሚሰናዳው በዚህ ውድድር ላይ ሀገራችን ኢትዮጵያ በተወዳዳሪነት መካፈል ባትችል ሁለት አለም አቀፍ ዳኞች ግን ተወክለው በውድድሩ ላይ እንደሚካፈሉ ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ አመላክቷል።
በኢንተርናሽናል ረዳት ዳኝነት ያለፉትን አምስት ዓመታቶች በማገልገል ላይ የሚገኘው ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ፋሲካ የኋላሸት ለሁለት ጊዜያት የተሰጡትን ፈተናዎች በብቃት በማለፉ ከሀያ ስድስቱ ረዳት ዳኞች መካከል አንዱ መሆኑ ሲረጋገጥ በአምላክ ተሠማ ደግሞ በቫር ዳኝነት እንዲያገለግል ጥሪው ደርሶታል።
