መቻል ከአሰልጣኙ ጋር በስምምነት ተለያየ

መቻል ከአሰልጣኙ ጋር በስምምነት ተለያየ

ከአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ጋር የአንድ ዓመት ቀሪ ውል ያላቸው መቻሎች በስምምነት ተለያይተዋል።


በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ከፍተኛ ወጪ በማውጣት በርከት ያሉ ተጫዋቾችን በማምጣት ራሳቸውን በማጠናከር የሊጉን ዋንጫ ማንሳት የመጀመርያ ዕቅዳቸው ያደረጉት መቻል የታሰበው ሳይሆን ዝቅተኛ ውጤት አስመዝግበው ዓመቱን ማጠናቀቃቸው ይታወቃል።

ከሰሞኑ የክለቡ የበላይ ጠባቂዎች የክለቡ ውጤት ማጣት ምክንያቱ ምን እንደሆነ ሲገመግሙ የቆዮ ሲሆን ቀሪ የአንድ ዓመት ውል ካላቸው አሰልጣኝ ገብረ ክርስቶስ ጋር በመለያየት አዲስ አሰልጣኝ ለመቅጠር መወሰናቸውን ሰምተናል። ክለቡ ከአሰልጣኝ ገብረክርስቶን ዛሬ ጠርቶ ንግግር በማድረግ በስምምነት ለመለያየት የተስማሙ መሆናቸውን አረጋግጠናል።

በሌላ ዜና ክለቡ ከዋና አሰልጣኙ ብቻ ጋር ሳይሆን አጠቃላይ ሙሉ የአሰልጣኞች ቡድኑ አባላት የሆኑት ረዳት አሠልጣኙ ደምሰው እና የግብ ጠባቂዎች አሠልጣኝ በለጠን እንደሚያነሳ እንዲሁም ከቴክኒክ ዳሬክተሩ ኤሊት ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ጋር ጭምር እንደሚለያይ ታውቋል።

ክለቡ በቀጣዮቹ ቀናት አጠቃላይ የአሰልጣኝ አባላቱን በአዲስ መልክ እንደሚያዋቅር ያገኘነው መረጃ ያመላከልታል።