በሰሜን ለንደኑ ክለብ ትልቅ ተስፋ የተጣለባቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን ታዳጊዎች

በሰሜን ለንደኑ ክለብ ትልቅ ተስፋ የተጣለባቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን ታዳጊዎች

መንትዮቹ ትውልደ ኢትዮጵያውን ወደ አርሰናል ከአስራ ስምንት ዓመት በታች ቡድን አደጉ።

በቅርብ ዓመታት ውስጥ ቡካዬ ሳካ፣ ኤሚል ስሚዝ ሮው፣ ማይልስ ልዊስ ስኬሊ፣ ኢታን ንዋኔሪ፣ ማክስ ዶውማን፣ ቺዶ ኦቢ ማርቲን እና አይደን ሄቨን የመሳሰሉ ተስፈኞች ያፈራው የአርሰናሉ ‘ሃላ ኢንድ’ አሁን ደግሞ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተስፈኞች ለዋናው ቡድን እያዘጋጀ ይገኛል፤ መንትዮቹ የአብስራ ሜሮን እና ቃልአብ ሜሮን !


ከ2013 እስከ 2019 በአርሰናል ቤት ቆይቶ የነጥብ ጨዋታ ሳያከናውን ከቡድኑ ጋር ከተለያየው ጌድዮን ዘላለም በኋላ በእንግሊዝ ምድር ትልቅ ተስፋ የተጣለባቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሆኑት መንትዮቹ የአብስራ ሜሮን እና ቃልኣብ ሜሮን በወሩ መጀመርያ ላይ አስራ ስድስተኛ ዓመታቸው የደፈኑ ሲሆን በእንግሊዝ ከአስራ አምስት ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን እና በአርሰናል ወጣት ቡድን ባሳዩት ብቃት ከወዲሁ ትኩረት ስበዋል።

በ2022/23 የውድድር ዓመት ከታዳጊ ቡድኑ ጋር ‘የናሽናል ካፕ’ አሸናፊ የነበሩት ወንድማማቾቹ በአሁኑ ሰዓት በአርሰናል ከአስራ ስምንት ዓመት በታች ቡድን ተካተው ለቅድመ ውድድር ዝግጅት ወደ ጀርመን ያቀኑ ሲሆን የአብስራ ሜሮንም ከወልፍስበርግ ጋር በተደረገው ጨዋታ ተሳትፏል። በአካዳሚው ዳይሬክተር ቀውላላው ጀርመናዊው ፔር ሜርቲሳከር ጨምሮ የበርካታ የክለቡ ደጋፊዎች ትኩረት የሳቡት ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ
ከግዙፉ ትጥቅ አምራች ናይኪ ጋር የረዥም ጊዜ የማስታወቅያ ስምምነት የተስማሙ ሲሆን በቅርብ ዓመታት በዋናው ቡድን ደረጃ ይጫወታሉ ተብለው ከሚገመቱ ተስፈኛ ታዳጊዎች ይጠቀሳሉ።

የአብስራ ሜሮን በዋነኝነት መስመር ተከላካይነት እንዲሁም የመስመር ተጫዋች ሆኖ መጫወት የሚችል ሲሆን ከዓመታት በፊት በሚሊዮን የሚቆጠር ዕይታ ባገኘው አንድ ተንቃሳቃች ምስል አማካኝነት የብዙዎች ትኩረት አግኝቶ ነበር። እንደ መንትያ ወንድሙ በትልቅ የታዳጊዎች ውድድር ላይ የእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድንና አሳዳጊ ክለቡ አርሰናልን የወከለው ቃልአብ ሜሮን የአማካይ ክፍል ተሰላፊ ሲሆን ቡድናቸው የናሽናል ካፕ ዋንጫ ባሳካበት ወቅት ወሳኝ ከነበሩ ተሰላፊዎች አንዱ ነው።

የነ ቡካዬ ሳካ፣ ማይልስ ልዊስ ስኬሊ እና ኢታን ንዋኔሪ ፈለግ ተከትለው በዋናው ቡድን ደረጃ የመጫወት አቅም እንዳላቸው የሚነገርላቸው የአስራ ስድስት ዓመት ትውልደ ኢትዮጵያውያኖቹ የውድድር ዓመቱ ከአስራ ስምንት ዓመት በታች ቡድን ውስጥ በመጫወት ያሳልፉታል ተብሎ ይጠበቃል።

ከጊዜ ወደ ጊዜ በታላላቅ የአውሮፓ ክለቦች የሚጫወቱ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ቁጥር እየተበራከተ ይገኛል፤ በጣልያኑ ቶሪኖ ዋናው ቡድን የሚጫወተው አሮን ሲማግሊቼላ፤ ባለፈው የውድድር ዓመት በጣልያኑ ጄኖዋ የውሰት ቆይታ አሳልፎ በአሁኑ ሰዓት ወደ ማካቢ ሀይፋ የተመለሰው ሊዮር ካሳ፤ በባየር ሊቨርኩሰን ታዳጊ ቡድን የሚጫወተው ነቤ ሲራክ ዶሚኒክ እና በኢንትራክት ፍራንክፈርት ታዳጊ ቡድን የሚጫወተው ናትናኤል አብርሀ ከብዙዎቹ ይጠቀሳሉ።