ኬንያዊው የግብ ዘብ ፈረሰኞቹን ለመቀላቀል ንግግር እያደረገ ይገኛል።
በዛሬው ዕለት አቤል ያለውን በማስፈረም የሻሂዱ ሙስጠፋን ውል ለተጨማሪ ዓመት ያራዘሙት ቅዱስ ጊዮርጊሶች አሁን ደግሞ ኬንያዊውን ግብ ጠባቂ ለማስፈረም ንግግር እያደረጉ እንደሆነ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል። ፈረሰኞቹን ለመቀላቀል እየተነጋገረ የሚገኘው ተጫዋች ደግሞ ኬንያዊው ፋሩክ ሺካሎ ነው።
የኤስ ሲ ባንዳሪ ተጫዋች የሆነው እና በአሁኑ ሰዓት ሀገሩ ኬንያ ከጋምቢያ እና ሲሼልስ ጋር ለምታደርጋቸው የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ለመሳተፍ በሀራምቤ ስታርስ ስብስብ የሚገኘው ተጫዋቹ ከፈረሰኞቹ ጋር እያደረገው የሚገኘው ድርድር በስምምነት ለመቋጨት ከጫፍ ደርሷል። ከዚህ ቀደም በፖስታ ሬንጀርስ፣ ባንዳሪ፣ ያንግ አፍሪካንስ፣ ኬ.ኤም.ሲ ( Kinondoni Municipal Council) እና Mtibwa Sugar መጫወት የቻለው ይህ ግብ ጠባቂ ከፓትሪክ ማታሲ ቀጥሎ ፈረሰኞቹን ለማገልገል የተቃረበ ኬንያዊ ግብ ጠባቂ ነው።
የኬንያ ሚዲያዎች የግብ ዘቡ ወደ አዲስ አበባ ከቀናት በኋላ እንደሚሄድ እና ለፈረሰኞቹ እንደሚፈርም እየዘገቡት እንደሆነ ሲታወቅ ከዚህ መረጃ በተጓዳኝ የፈረሰኞቹ የቦርድ አመራር ከንግግር ባለፈ አሁናዊ ውሳኔ ዛሬ የሚጠበቅ ይሆናል።