በአሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል ወደ ሚመራው ካምፓላ ኩዊንስ አቅንታ የነበረችው አጥቂዋ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሳ ለጦሩ ፊርማዋን አኑራለች።
ቀደም ብለን ባስነበብናችሁ ዜና ማዕድን ሳህሉ ለካምፓላ ኩዊንስ ለመጫወት ተስማምታ ወደ ዩጋንዳ ብታመራም ከሦስት ጨዋታዎች በላይ ከቡድኑ ጋር ሳትቆይ ወደ ሀገር ቤት ተመልሳ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መፈረሟን ነግረናችሁ ነበር።
አሁን ባገኘነው መረጃ ደግሞ በይርጋጨፌ ቡና ፣ ሲዳማ ቡና ፣ አርባምንጭ ከተማ ለተከታታይ አራት ዓመታት ደግሞ በሀዋሳ ከተማ መለያ ቆይታን ካደረገች በኋላ ወደ ዩጋንዳ ተጉዛ በአሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል ለሚመራው ካምፓላ ኩዊንስ የመጀመሪያ ጨዋታዎችን ማድረግ የቻለችው አጥቂዋ ቱሪስት ለማ እንደ ማዕድን ሳህሉ ሁሉ ግልጽ ባልሆነ ምክንያት ከቡድኑ ጋር ተለያይታ ወደ ሀገር ቤት በመመለስ ለመቻል ለመጫወት ፊርማዋን ማኖሯን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።