በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ5 ኛው ሳምንት የምድብ ሁለት የመጨረሻ ቀን ጨዋታዎች ላይ አዳማ ከተማ ኢትዮጵያ ቡናን ስያሸንፍ የሸገር ከተማና ሀድያ ሆሳዕና ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
አዳማ ከተማ 1-0 ኢትዮጵያ ቡና
አዳማ ከተማ በተሻለ የኳስ ቁጥጥር ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ በፈጣን ሽግግሮች የተንቀሳቀሱበት የመጀመርያው አጋማሽ የጠሩ የግብ ዕድሎች ያላስመለከተ ነበር። በሁለቱም ቡድኖች በኩልም አንድ አንድ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ሲደረግ የተሻለ ብልጫ በነበራቸው አዳማ ከተማዎች ቢንያም አይተን ከርቀት አክርሮ ያደረገው ሙከራ እንዲሁም በኢትዮጵያ ቡና በኩል አቡበከር አዳሙ በግንባር ያደረገው ሙከራ ይጠቀሳሉ።

በአዳማ ከተማ ብልጫ የቀጠለው ሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ የተደረገበት ሲሆን በ58′ ደቂቃም ነቢል ኑሪ በረዥሙ ተሻግራ የቡናማዎቹ ተጫዋቾች በአግባቡ ያላራቋት ኳስ ከሳጥን ውጭ አግርሮ በማስቆጠር አዳማዎችን መሪ ማድረግ ችሏል። ከግቧ መቆጠር በኋላ አዳማዎች በብዙአየሁ ሰይፉ አማካኝነት ግብ ለማስቆጠር ጥረት ስያደርጉ አማኑኤል አድማሱ በሳጥን ውስጥ ያገኛትን ኳስ መቶ አላዛር ማርቆስ የመለሳት ኳስም ቡናማዎቹን አቻ ለማድረግ ተቃርባ ነበር። በ73′ ኛው ደቂቃ የኢትዮጵያ ቡናው በፍቃዱ ዓለማዮህ በቀይ ካርድ ከሜዳ የወጣ ሲሆን ተቀይሮ የገባው ሀብታሙ አሸናፊ በመጨረሻው ደቂቃ ያልተጠቀመባት ኳስም በቡናማዎቹ በኩል ትጠቀሳለች። ጨዋታው በአዳማ ከተማ የአንድ ለባዶ አሸናፊነት መጠናቀቁ ተከትሎም ቡድኑ በሊጉ ግብ ያላስተናገደ ብቸኛው ክለብ በመሆን የ5ኛው ሳምንትን አጠናቋል።
ሸገር ከተማ 1-1 ሀድያ ሆሳዕና
በአካላዊ ፍልምያዎች የታጀበ ብርቱ ፉክክር የተደረገበት የመጀመርያው አጋማሽ ሳቢ እንቅስቃሴ ያስመለከተ ነበር። በጅማሮው ብልጫ የነበራቸው ሸገር ከተማዎች ያሬድ መኮንን ካደረጋት ዒላማዋን ያልጠበቀች ሙከራ በኋላ በሀድያ ሆሳዕና ሳጥን የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ ያገኙት ፍፁም ቅጣት ምት ሄኖክ አዱኛ ወደ ግብነት ቀይሮ መሪ አድርጓቸዋል። ሸገር ከተማዎች ግቧን ካስቆጠሩ በኋላም ጅቤሳ ሚኤሳ ከቀኝ መስመር አሻግሯት ያሬድ መኮንን ከግቡ አፋፍ ብቻውን ሆኖ ባመከናት አስቆጪ ሙከራ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። በቀሩት ደቂቃዎች ብልጫ የነበራቸው ሀድያ ሆሳዕናዎች በፀጋዓብ ግዛው አማካኝነት ካደረጓቸው ሁለት ዒላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች በኋላ በአጋማሹ መገባደኛ ደቂቃ የአቻነቷን ግብ አስቆጥረዋል። አሸናፊ ኤልያስ ከቀኝ መስመር አሻግሯት ብሩክ በየነ በጥሩ መንገድ ካበረደ በኋላ ከመረቡ ጋር ያዋሀዳት ኳስም ነብሮቹን አቻ ያደረገች ግብ ነች።

ሁለቱም ቡድኖች እየተፈራረቁ ብልጫ የወሰዱበት ሁለተኛው አጋማሽ የጠሩ የግብ ዕድሎች ያልተደረጉበት ነበር። ሆኖም በሀድያ ሆሳዕናዎች በኩል እዮብ አለማዮህ ከርቀት ባደረገው እንዲሁም ተቀይሮ የገባው ኤልያስ አሕመድ አክርሮ መቶት ባህሩ ነጋሽ በጥሩ ቅልጥፍና በመለሰው ኳስ፤ በሸገር ከተማ በኩል ደግሞ ሄኖክ አዱኛ ከቆመ ኳስ እንዲሁም ጀቤሳ ምኤሳ ያደረጓቸው ሙከራዎች ይጠቀሳሉ። ጥሩ ፉክክር የተደረገበት ጨዋታም በሁለተኛው አጋማሽ ግብ ሳይቀጠርበት በአቻ ውጤት ተጠናቋል።



