ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች|  የ22ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች| የ22ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች

22ኛው ሳምንት የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ በሚደረጉ አራት መርሐ-ግብሮች ይቀጥላል፤ ጨዋታዎቹን የተመለከቱ መረጃዎችም እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል

ኢትዮጵያ ቡና ከ ባህር ዳር ከተማ

 

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ22ኛው ሳምንት መርሃ-ግብር የሚገናኙት ኢትዮጵያ ቡና እና ባህር ዳር ከተማ ከደረጃ ሰንጠረዡ አካፋይ ከፍ የሚያደርጋቸውን ወደ ሜዳ ይገባሉ። ኢትዮጵያ ቡና ካለፉት አምስት ጨዋታዎች በሁለቱ ድል ቀንቶት፣ በአንዱ አቻ ተለያይቶ በሁለቱ ሽንፈት ያስተናገደ ሲሆን በአሁኑ ወቅት አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በ26 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በተለይም ክለቡ ባደረጋቸው 20 ጨዋታዎች 17 ጎሎችን አስቆጥሮ 20 ጎሎች የተቆጠሩበት በመሆኑ የተከላካይ ክፍሉ ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ማረም በዛሬው ጨዋታ ወሳኝ ይሆናል።

በአንጻሩ ተጋጣሚው ባህር ዳር ከተማ በ27 ነጥብ 8ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ የሚገኝ ሲሆን ካለፉት አምስት ጨዋታዎች ማግኘት ካለበት 15 ነጥብ ውስጥ ማሳካት የቻለው 6 ነጥብ ብቻ መሆኑ (1 ድል፣ 1 ሽንፈትና 3 አቻ) ቡድኑ በውጤት መዋዥቅ ውስጥ እንዳለ ያሳያል። ባህር ዳር በሊጉ ካደረጋቸው 21 ጨዋታዎች 12ቱን በአቻ ውጤት ማጠናቀቅ ችሏል ይህም በሊጉ ብዙ የአቻ ውጤት ያስመዘገበ ቡድን ያደርገዋል። ሁለቱም ክለቦች ወደ ሊጉ አናት ለመጠጋት የነገው ሦስት ነጥብ እጅግ አስፈላጊያቸው በመሆኑ ጨዋታው ጥሩ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ለ13 ጊዜያት ተገናኝተው ባህር ዳር ከተማ 5 ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ 2 ጊዜ ድል ሲያደርጉ ስድስቱ ጨዋታዎች አቻ የተጠናቀቁ ናቸው። በግንኙነታቸውም ባህር ዳር ከተማ 21 ኢትዮጵያ ቡና 19 ግቦችን አስቆጥረዋል።

 

ሲዳማ ቡና ከ ፋሲል ከነማ

 

የሲዳማ ቡና እና የፋሲል ከነማ ጨዋታ የሊጉን መሪነት ለማጽናትና ወደ መሪነቱ ለመጠጋት የሚደረግ ወሳኝ እና ተጠባቂ ፍልሚያ ነው። ሲዳማ ቡና በአሁኑ ወቅት በ39 ነጥብ የደረጃ ሰንጠረዡን በአንደኝነት እየመራ የሚገኝ ሲሆን በ21 ጨዋታዎች ያስቆጠራቸው 26 ጎሎች እና የተቆጠሩበት 11 ጎሎች ብቻ መሆናቸው በሊጉ ሚዛናዊ እና ጠንካራ የሚባል ተከላካይ ያለው ቡድን መሆኑን ያሳያል። ሲዳማ ቡና ካለፉት አራት ተከታታይ ጨዋታዎች በኋላ ባሳለፍነው ሳምንት የከተማ ተቀናቃኙን ሀዋሳ ከተማን በደርቢ ጨዋታ 2 ለ 1 በማሸነፍ ወደ ድል መመለሱ ለዛሬው ጨዋታ ትልቅ ስነ-ልቦናዊ መነቃቃትም ይፈጥርለታል።።

በተቃራኒው ፋሲል ከነማ በ33 ነጥብ በ4ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ ወደ ጨዋታው ይቀርባል። ክለቡ ካደረጋቸው 21 ጨዋታዎች 8 ድሎችን ቢያስመዘግብም ካለፉት አምስት ጨዋታዎች በሦስቱ በተከታታይ ሽንፈት ማስተናገዱ (3 ሽንፈት፣ 1 ድል፣ 1 አቻ) ቡድኑ በከፍተኛ የውጤት መዋዥቅ ውስጥ እንደሚገኝ ያሳያል። በተለይም በ21 ጨዋታዎች ያስቆጠረው የጎል መጠን 16 ብቻ መሆኑ (በአማካይ በጨዋታ 0.76 ጎል) የፊት መስመሩ ላይ ያለውን ድክመት በግልጽ የሚያሳይ ነው። ፋሲል ከነማ ከሊጉ መሪ ጋር በሚያደርገው በዚህ ጨዋታ ካለበት ተከታታይ ሽንፈት አገግሞ ወደ ሻምፒዮናነቱ ፉክክር ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርግ ይጠበቃል። የመጀመሪያ ዙር ግንኙነታቸው በረከት ግዛው ባስቆጠረው ብቸኛ ግብ ዐፄዎቹ 1-0 በሆነ ውጤት ድል ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።

በሊጉ 17 ጊዜ የተገናኙት ሁለቱ ቡድኖች ፋሲል ከነማ አስር ጨዋታዎች በማሸነፍ የበላይ ሲሆን ሲዳማ ቡናዎች አምስት ጨዋታዎች ማሸነፍ ሲችሉ ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል። ፋሲል ከነማ 25 ግቦች ሲያስቆጥር ሲዳማ ቡና ደግሞ 17 አስቆጥሯል። (የተሰረዘው የ2012 የውድድር ዓመት አልተካተተም)

 

አርባ ምንጭ ከተማ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ

 

በቅርብ ሳምንታት ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ የሚገኙ አርባ ምንጭ ከተማዎች ከወራጅ ቀጠናው የሚወጡበት ዕድል ለማለምለም ወደ ጨዋታው ይቀርባሉ። ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በውጤት ረገድም መሻሻሎችን ያስመለከቱን አዞዎቹ ካደረጓቸው አምስት ጨዋታዎች መካከል በሁለቱ ድል ቀንቷቸው ሶስቱን ደግሞ በአቻ ውጤት ማጠናቀቅ ችለዋል። ከሰንጠረዡ ግርጌ ለመላቀቅ የሚያደርጉት ጉዞ ለማሳለጥም ወደ ማጥቃት ያደላ አቀራረብ ይዘው እንደሚገቡ ይጠበቃል።

በአንጻሩ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በደረጃ ሰንጠረዡ አጋማሽ 7ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ የተረጋጋ ጉዞ እያደረገ ይገኛል። የቡድኑ ዋነኛ ጥንካሬ እጅግ ጥብቅ የሆነውና በ21 ጨዋታዎች 11 ግቦችን ብቻ ያስተናገደው የተከላካይ ክፍሉ ነው። ምንም እንኳን ቡድኑ ካለፉት አምስት ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው በአንዱ ብቻ ሲሆን ጨዋታዎችን በአቻ ውጤት የማጠናቀቅ ክፍተቱን መቅረፍ ይኖርበታል። ዛሬም በመጀመሪያው ዙር 3 ለ 1 ያሸነፈውን አርባ ምንጭን በድጋሚ በመርታት ወደ መሪዎቹ ለመጠጋትና በሊጉ ያለውን ጠንካራ የመከላከል ብቃት ለማስቀጠል ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚያደርግ ይገመታል።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 19 ጊዜ ተገናኝተዋል። ኤሌክትሪክ 8 ሲያሸንፍ አርባምንጭ 6 አሸንፏል፤ በአምስት ጨዋታ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። የበላይ የሆኑት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች 25 ግቦችን ሲያስቆጥሩ አርባምንጭ ከተማዎች ደግሞ 22 ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል።

በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል ያሬድ የማነ በቅጣት ምክንያት አይሰለፍም በተጨማሪም የሄኖክ ገብረህይወት መሰለፍ አጠራጣሪ ነው። አርባምንጭ ከተማዎች አበበ ጥላሁን በቅጣት ምክንያት አያሰልፉም ከዚህ በተጨማሪም አዳዲስ ፈራሚዎቹ ለዛሬው ጨዋታ አይደርሱም።

 

ወላይታ ድቻ ከ ሀዋሳ ከተማ

 

የወላይታ ድቻ የዘንድሮ የውድድር ዘመን ጉዞ በውጣ ውረድ የተሞላ ቢሆንም በቅርብ ሳምንታት እያሳየ ያለው መነቃቃት ግን ለተጋጣሚዎቹ ቀላል ተፎካካሪ እንዳልሆነ አሳይቷል። ቡድኑ በሊጉ ግርጌ 17ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ ቢገኝም ካለፉት ሁለት ጨዋታዎች ያስመዘገባቸው ስድስት ነጥቦች በተለይም በመቻል ላይ ያስቆጠራቸው አራት ጎሎች የክለቡን የአጥቂ መስመር ዳግም መወለድ ያበሰሩ ነበሩ። ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት የጀመሩትን የሞት ሽረት ትግል ለማጠናከርም የሊጉን አናት ለመቆናጠጥ እያለሙ ወደ ሜዳ ከሚገቡት ሀዋሳዎች ብርቱ ፍልሚያ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ሀዋሳ ከተማ በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ 2ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ የዋንጫ ተፎካካሪነት ላይ የሚገኝ ቡድን ነው። በሊጉ 36 ነጥቦችን በመሰብሰብ ከመሪው ሲዳማ ቡና በሦስት ነጥብ ብቻ ዝቅ ብሎ የሚገኘው ሀዋሳ ባለፈው ሳምንት ከከተማ ተቀናቃኙ ሲዳማ ቡና ጋር በነበረው ጨዋታ ከደረሰበት ሽንፈት ለማገገም ከወላይታ ድቻ ጋር ይፋለማል። በ21 ጨዋታዎች 24 ግቦችን ያስቆጠረውና ሚዛናዊ የሆነ የጨዋታ ፍሰት ያለው ይሄው ቡድን ዛሬ የሊጉን መሪነት ለመረከብ በሚያደርገው ጉዞ የማጥቃት የበላይነቱን ይዞ እንደሚገባና ለድቻ ተከላካዮች ፈታኝ ምሽት እንደሚሆንባቸው ይገመታል።

በወላይታ ድቻ በኩል ኬኔዲ ከበደ በጉዳት የማይኖረው ብቸኛ ተጫዋች ነው፤ ሀዋሳ ከተማዎች ከጉዳትም ሆነ ከቅጣት ነፃ የሆነውን ስብስብ ይዘው ይቀርባሉ።

ሁለቱም ቡድኖች በሊጉ እስከ አሁን ለ23 ጊዜያት ያህል የተገናኙ ሲሆን ሀዋሳ ከተማ 9 ጊዜ ወላይታ ድቻ ደግሞ 7 ጊዜ አሸንፈዋል። በሰባት አጋጣሚዎች ደግሞ አቻ ሲለያዩ ፤ ሀዋሳ ከተማ ደግ 28 ግቦችን ወላይታ ድቻ ደግሞ 23 ጎሎችን በግንኙነታቸው አስቆጥረዋል።