ከማላዊ አቻው ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ከሚያደርገው የዋልያዎቹ ስብስብ አንድ ተጫዋች ከስብስቡ ውጪ መሆኑን አውቀናል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከማላዊ አቻው ጋር ግንቦት 29 እና ሰኔ 2 በድሬዳዋ ስታዲየም የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ ቀጠሮ ተይዟል። ለዚህም እንዲረዳቸው እንደ ዋልያዎቹ ሁሉ ማላዊም ለ23 ተጫዋቾች ጥሪ ማድረጋቸውን ገልፀንላችሁ ነበር።
አሁን በብሔራዊ ቡድኑ የተሰማው አዲስ ነገር የሲዳማ ቡናው የመስመር አጥቂ መስፍን ታፈሰ ቡድኑ ትናንት ከአዳማ ከተማ ጋር በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ባደረገው ጨዋታ ገና በመጀመርያዎቹ አስራ አምስት ደቂቃዎች ውስጥ የጡንቻ መሳሳብ ጉዳት አስተናግዶ ተቀይሮ ለመውጣት ተገዶ ነበር። የጉዳቱ ሁኔታ ጨዋታውን ማስቀጠል ያላስቻለው መስፍን ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ሶከር ኢትዮጵያ “ጉዳትህ ከብሔራዊ ቡድን ውጭ ያደርግ ይሆን?” ብላ ላቀረበችለት ጥያቄ “እኔ እንጃ ሕመም አለው የምችለውን ለማድረግ እሞክራለሁ።” ብሎን ነበር።
ሶከር ኢትዮጵያ አሁን ባገኘችው መረጃ መስፍን ቡድኑ ወዳረፈበት ሆቴል በመጓዝ ሪፖርት ያደረገ ሲሆን አሰልጣኝ ዮሐንስም የሕመሙን ሁኔታ በመረዳት ዕረፍት እንዲያደርግ እንደፈቀዱለት ሰምተናል። መስፍንም ክለቡ ሲዳማ ቡና የሰጠውን ዕረፍት ተከትሎ በአሁን ሰዓት ወደ ትውልድ ሀገር ሀዋሳ እያቀና መሆኑንም ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
አሰልጣኝ ዮሐንስ በመስፍን ምትክ ማንን ወደ ስብስባቸው ይቀላቅላሉ የሚለውን መረጃውን እንዳገኘን ወደ እናንተ እናደርሳለን።

