በ ኢዝ- አሻራ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር የክለቦችን የክፍያ ጣሪያ (Salary Cap) አስመልክቶ ከዚህ ቀደም ያወጣውን መመሪያ በሙሉ ድምፅ መሻሩን በይፋ አሳውቋል። ይህ ውሳኔ በብዙዎች “መመሪያው ተሰረዘ” ብለው የሚያዩት ጉዳይ ብቻ አይደለም፤ ይህ ውሳኔ በብዙዎች ዘንድ እንደ ነፃ ገበያ ማበሰሪያ ቢታይም፣ ከጀርባው ግን በኢትዮጵያ እግር ኳስ የፋይናንስ እና የአመራር ውድቀት ላይ በርካታ ጥያቄዎችን አስነስቷል። በእርግጥም የሚያነሳው ጥያቄ የኢትዮጵያ ፕሮፌሽናል እግር ኳስ ወደ ዘላቂ የንግድ ሞዴል እየተሸጋገረ ነው ወይስ አሁንም በድጎማና በወቅታዊ ወጪ ላይ የተመሰረተውን አሠራር እየቀጠለ ነው? የሚለውን ነው።
የደመወዝ ጣሪያው ዓላማ ምን ነበር?
- በዓለም አቀፍ የስፖርት ኢኮኖሚ የደመወዝ ጣሪያ ዋና ዓላማዎች የመነጨ መመሪያው ሲወጣ ዋና ዓላማው የክለቦችን የፋይናንስ ጤንነት መጠበቅ፣ ያለአግባብ የሚናረውን የተጫዋቾች ደሞዝ ማረጋጋት እና በበጀት አቅም መካከል ያለውን ልዩነት በማጥበብ ፍትሃዊ ውድድር (Competitive Balance) መፍጠር ነበር። የክለቦችን የፋይናንስ ዘላቂነት ለመጠበቅ፣ ከአቅም በላይ የሚደረግ፣የተጫዋች ወጪን ለመከላከል ፣ የውድድር ፍትሃዊነትን ለማሳደግ እንዲሁም የክለቦችን የፋይናንስ አስተዳደር ማዘመን ነበር፡፡
ለምን ውድቀት አጋጠመው ?
መሠረት አልነበረውም
ሕጉ ሲወጣ ከስሩ ሊደግፉት የሚችሉ የዲጂታል የፋይናንስ መቆጣጠሪያ ሥርዓቶች፣ ግልጽ የባንክ አሰራሮች እና ነፃ የኦዲት መዋቅሮች አልነበሩም። ያለ ጠንካራ መሠረት በወረቀት ላይ ብቻ የተጣለ ደንብ በመሆኑ፣ የመጀመሪያው የገበያ እና የክለቦች ጫና ሲመጣ በቀላሉ ሊናድ ችሏል።
በጓሮ በር በሚደረጉ ክፍያዎች (“Under the Table” Payments)
አሸዋ ላይ የተሰራ ቤት በውኃ እንደሚሸረሸረው ሁሉ፣ ይህ መመሪያም በጥሬ ገንዘብ (Cash) እና በጓሮ በር በሚደረጉ ክፍያዎች ተሸረሸረ። በዲጂታል መንገድ ክፍያዎችን መቆጣጠር አለመቻሉ፣ ክለቦችና ወኪሎች ሕጉን በቀላሉ እንዲሸውዱት እና መመሪያው ውስጡ ባዶ እንዲሆን አድርጎታል።
የማስፈጸም አቅም (Solid Enforcement) አልነበረውም
ቤቱን አጽንቶ የሚይዝ የኮንክሪት ካስማ ከሌለ እንደሚፈርስ ህንፃ ሁሉ ሕጋዊ ማስገደጃና ወጥና ጥብቅ የሆነ ቅጣት አልነበረም ማለት ያቻላል። መመሪያውን በጣሱ ክለቦች ላይ የማያወላውል እርምጃ መወሰድ ባለመቻሉ፣ ሕጉ ክብደት እንዲያጣና በስተመጨረሻም በሙሉ ድምፅ እንዲሻር መንገድ ጠርጓል።

መመሪያው ለምን ከ2ዓመት በላይ መሄድ አልቻለም ?
የመመሪያው መሻር ብቻውን የፖሊሲው ስህተት ነበር ብሎ ለመደምደም በቂ ባይሆንም የፖሊሲ ውድቀት ከፖሊሲው ይልቅ አተገባበሩ ጠንካራ የክትትል ስርዓትና ቁርጠኝነት ጋር ይያያዛል።
የታችኛው ገበያ ጫና፡ የተጫዋቾች ወኪሎች እና ክለቦች መመሪያውን የሚሸውዱበት አማራጭ መንገዶችን በመፍጠራቸው።
የተቋማዊ ቁርጠኝነት ማነስ፡ መመሪያውን የጣሱ ክለቦችን በወሳኝ ደረጃ የመቅጣት እና የመቆጣጠር የህግ እና የፖሊስ ስልጣን/አቅም አለመኖሩ።
ያልተዘጋጀ አሰራር፡ ክለቦች ግልፅ የሆነ የፋይናንስ ሪፖርት ማቅረብ የሚያስችላቸው የቴክኖሎጂ እና የሂሳብ አያያዝ መዋቅር ሳይዘረጋ መተግበሩ። ቢነሳም አሁንም ቢሆን መነሳትና መፈተሸ ያለበት
- ° ክለቦች ለመመሪያው በቂ ዝግጅት ነበራቸው ወይ?
- ° የክፍያ መረጃዎች በግልፅነት ይመዘገቡ ነበር ወይ ?
- ° በቂና ጠንካራ የኦዲትና የቁጥጥር ስርዓት ተዘጋጅቶ ነበር ወይ ?
- ° የዲጂታል የፋይናንስ መረጃ ስርዓትስ ነበር ? የሚሉት ናቸው
የማን ክፍተት ነው?
የስፖርት ሪፎርም የአንድ ተቋም ብቻ ኃላፊነት አይደለም። ፖሊሲ አውጪዎች, የሊጉ አስተዳደር,ክለቦች, የቁጥጥር አካላት, የፋይናንስ ባለሙያዎች, የዲጂታል ስርዓት ገንቢዎች ሁሉም የኒጋሩት ኃላፊነቶች አሏቸው።በዚህ ውስጥ ዋነኛ ተዋናዮቹ የፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር፡ መመሪያውን ከማውጣቱ በፊት በቂ የቅድመ ዝግጅት ስራ፣ የዲጂታል መቆጣጠሪያ መድረክ እና የክትትል ስልት አለመዘርጋቱ። የክለቦች አመራሮች፡ ለረጅም ጊዜ ስትራቴጂያዊ እቅድ ከመገዛት ይልቅ፣ ለጊዜያዊ ውጤት ብለው ህግጋትን ለማቅለል እና መመሪያውን ለመጣስ መጠቀማቸው። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፡ የቁጥጥር እና የቁጥጥር ማእቀፎችን (Regulatory Frameworks) በበቂ ሁኔታ አለማጠናከሩ።
ውሳኔው የ”ከእጅ ወደ አፍ” አመራር ዑደትን ያስቀጥላልን?
ምን ምን ተቃርኖዎችስ አሉት ?
ይህ ውሳኔ እንደ ነጋዴ አክሲዮን ማህበር መመራት የሚገባውን የፕሪሚየር ሊግ አወቃቀር ወደ ኋላ የሚመልስ ስጋት አለው። የደሞዝ ካፑ መነሳቱ ክለቦች የሚያገኙትን አብዛኛውን በጀት ለወቅታዊ ወጪዎች (ደሞዝ፣ አበል እና የጉዞ ወጪ) እንዲያውሉ ያፋጥነዋል። ይህም ስኬትን በኢንቨስትመንት ትርፋማነት (ROI) ሳይሆን በውድድር ተሳትፎ እና በመንግስት ድጎማ ብቻ የሚለካበትን፣ ለረጅም ጊዜ የታገገልነውን “ከእጅ ወደ አፍ” የሆነ የአመራር ዑደት እንደገና ያጠናክረዋል።
የውሳኔው ተቃርኖዎች
ለዘላቂ ሀብት ግንባታ (Asset Building) ያለው ተቃርኖ የደሞዝ ጣሪያው መነሳት ለሀገሪቱ እግር ኳስ መሰረታዊ ለሆኑት ለረጅም ጊዜ ሀብት ግንባታዎች ትልቅ እንቅፋት ይፈጥራል።
ታዳጊ አካዳሚዎች (Youth Academies): ክለቦች ያለቸውን ውስን በጀት ለዋናው ቡድን ደሞዝ ስለሚያወጡት፣ ለታዳጊዎች ስልጠና የሚሆን ገንዘብ ያጣሉ።
ዳታ እና ቴክኖሎጂ (Data & Analytics): ዘመናዊ የስካውቲንግ እና የመረጃ ቴክኖሎጂዎችን ለመገንባት የሚሆን በጀት አይኖርም።

የወደፊቱ መንገድ
የክፍያ ጣሪያው ሃሳብ በራሱ ጥሩና መልካም ጅምር ሆኖ መልሶ የወደቀው ያለ ዲጂታል መሠረተ ልማት እና ያለ ጥብቅ የፋይናንስ ቁጥጥር መተግበሩ በመሆኑ ህንጻውን ያለ መሠረት አሸዋ ላይ የመገንባት ያህል ነበር፡፡ ውጤቱም መመሪያው በአጭር ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ እንዲፈርስ ሆኗል መሻሩም ግልፅ በሆነ ሪፎርም አቅጣጫ ሳይደገፍ ክለቦች ወደነበሩበት “ከእጅ ወደ አፍ” የአሰራር ዑደት እንዲመለሱ እድል ሰጥቷቸዋል። ስለሆነም እውነተኛው ውድድር በተጫዋቾች ደመወዝ ብቻ እንደማይወሰን ታውቆ በረጅም ጊዜ የሊጉን እሴት የሚጨምሩ የታዳጊ አካዳሚዎች፣የተጫዋች ልማት ፣የዳታ አስተዳደር, የዲጂታል መሠረተ ልማት ፣ዘመናዊ የፋይናንስ ስርዓት ፣የንግድ ስትራቴጂ መቀየስና መተግበር ግድ ይላል፡፡

