ምፀት ወይንስ እውነታ ? የዋልያዎቹ ዓለቃ የዛሬው ንግግር ሲፈተሽ……

ምፀት ወይንስ እውነታ ? የዋልያዎቹ ዓለቃ የዛሬው ንግግር ሲፈተሽ……

እርሶ ቢሆኑ ምን ያደርጋሉ?!

የዋልያዎቹ ዓለቃ ወቀሳ ለመሰንዘር ተገቢው ሰው ናቸው…?

በ1990ዎቹ አጋማሽ ታዋቂ የነበረችውና የአሜሪካ-ራሽያ ዜግነት ባለቤት የሆነችው እውቋ ፀሀፊና ፈላስፋ አይን ራንድ እንዲህ ትላለች “እውነታውን ልንሸሽ እንችላለን ፤ ነገር ግን እውነታውን የመካዳችንን ውጤት ግን መሸሽ አንችልም” ይህ አባባል የዛሬውን የአሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌን ንግግር በሚገባ የሚገልፅ ይመስላል።

አሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌ ዛሬ ረፋድ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን 18ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ እንዲህ ሲሉ ተደመጡ”ብሔራዊ ቡድናችን የክለቦች ስብስብ ነው። ክለቦች ናቸው ብሔራዊ ቡድኑን አንድ የሚያደርጉት። ክለቦችን ማሳስበው ግብ ጠባቂዎችን የሚያፈሩበት መንገድ ይታሰብበት ከ18ቱ ክለቦች 16ቱ የውጪ ሀገር ግብ ጠባቂዎች ናቸው።”

አሰልጣኙ ያነሱት ሃሳብ በጣም አስደንጋጭ ነገርግን የሊጉ መራራ እውነት ሆኖ በመሰንበቱ እንደ መደበኛ ጉዳይ የተቆጠረ ነባራዊ ሃቅ ቢሆንም አሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌ ግን ይህን ሃሳብ በአደባባይ አንስተው ሌሎችን ለመውቀሱ የተገቡ ሰው የመሆናቸው ጉዳይ ግን አጠያያቂ ነው።

ለምን?

አሰልጣኝ ዮሀንስ በሁለት አጋጣሚዎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከማሰልጠናቸው ባለፈ በሊጉ ክለቦች በስልጠና የነበራቸው ቆይታ በሀገር ውስጥ ግብ ጠባቂዎች ስለነበራቸው እምነት የሚነግረን አለ።

አሰልጣኙ ባለፉት 10 ዓመታት ውስጥ ስድስት የሊጉን ክለቦች ማሰልጠን የቻሉ ሲሆን በሰሩባቸው ክለቦች እዚህ ግባ የሚባል ውጤት ማስመዝገብ ባይችሉም ለአዳዲስ ወጣቶች ተጫዋቾች ዕድል በመስጠት እና ተጫዋቾችን ከዚህ ቀደም ከሚታወቁባቸው ተፈጥሮአዊ ቦታቸው ውጭ ለማጫወት ያደርጓቸው የነበሩ ሙከራዎች ከውጤታማነታቸው ይልቅ የሚነሳላቸው ጥንካሬያቸው ነው።

አሰልጣኙ ሀገር በቀል ግብ ጠባቂዎች ላይ ስለነበራቸው ምልከታ በሰሩባቸው ክለቦች የነበረውን እውነታ በጥቂቱ እንፈትሽ ፤ ከዳግም የብሔራዊ ቡድን ሹመታቸው በፊት በመጨረሻው ክለባቸው ፋሲል ከነማ ሞይስ ፓዋቲን ፣ በሀዲያ ሆሳዕና ታፔ አልዛየርን ፣ በመቻል ክሌመንት ቦዬን ፣ በወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርስቲ አብዱልአዚዝ ኬይታን ፣ በመቐለ 70 እንደርታ ደግሞ ፊሊፕ ኦቮኖን ፣ በደደቢት ክሌመንት ቦዬን ተቀዳሚ ምርጫዎቻቸው ነበሩ ፤ እነዚህ ግብ ጠባቂዎች ታድያ ኢትዮጵያዊያን ነበሩን? አሰልጣኙ በክለብ ቆይታቸው በልዩነት የሚነሳው በድሬዳዋ ከተማ የስልጠና ቆይታቸው በሳምሶን አሰፋ/ፍሬው ጌታሁን ከመጠቀማቸው ውጭ እሳቸውም ዛሬ በምፀት እንደተናገሯቸው የሙያ አጋሮቻቸው የውጭ ሀገር ዜግነት ያለው ግብ ጠባቂ “አስመጪ” ነበሩ።

በተጨማሪነትም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ቀጥሎ አንጋፋ በሆነው መቻል ስፓርት ክለብ በነበራቸው ቆይታ ክለቡ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የውጭ ሀገር ግብ ጠባቂ አለፍ ሲልም የውጭ ሀገር ተጫዋች ያስፈረመው በእርሳቸው ጊዜ መሆኑ አሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌ በሀገራችን ግብ ጠባቂዎች ላይ ያላቸውን “ጠንካራ ዕምነት” የሚያሳይ ነው።

በተጨማሪም ቆይታ ባደረጉባቸው የሊጉ ክለቦች ለሀገሪቱ አንዳች ነገር ያበረክታሉ ተብሎ ተስፋ ከተጣለባቸው ግብ ጠባቂዎች መካከል ለአብነት መቐለ 70 እንደርታ ከከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪሚየር ሊግ እንዲያድግ ትልቅ ሚና የነበረው ሶፎንያስ ሰይፈ ቡድኑን ወደ ሊጉ ቢያበቃም ፊሊፕ ኦቮኖን አሰልጣኙ በማስቀደማቸው በዓመቱ ወንበር ለማሟቅ የተገደደበት ፣ በወልዋሎ ቤት እንዲሁ እጅግ አስደናቂ ጊዜያት ያሳለፈውን በረከት አማረ እንዲሁም በሀዲያ ሆሳዕና ቤት ባሳየው ድንቅ ብቃት በአንድ ወቅት በኢትዮጵያ እግር ኳስ እጅግ ተስፋ የተጣለበት ተስፈኛው የግብ ዘብ ያሬድ በቀለ እንዲሁ እድገታቸው እንዲገታና የራስ መተማመናቸው እንዲሸረሸር ምክንያት የነበረው ማነው ስንል አሁን በሌሎች የሊጉ አሰልጣኞች ላይ ጣታቸውን እየቀሰሩ ያሉት አሰልጣኝ ስለመሆናቸው ታሪክ ይመሰክራል።

እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ አሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌ ዛሬ ላይ ተነስተው እርሳቸው አሁን ላይ ለብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ ጥሪ አማራጭ ሲያጥራቸው ሌሎች መሰሎቻቸውን አሰራራችሁን ፈትሹ ቢጤ ምክር መለገሳቸው በየትኛውም አግባብ ውሃ የሚያነሳ ሃሳብ አይደለም።

አሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌ ከሌሎች የሙያ አጋሮቻቸው ጋር በመሆን በአሰልጣኞች ስልጠና በአሁኑ ወቅት በሊጉ እየሰሩ የሚገኙትን አብዛኞቹ አሰልጣኞችን በአጫጭር ስልጠናዎች (Refreshment Course) ሆነ በሌሎች ኮርሶች በእርሳቸው ስር በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ያለፉ እንደመሆናቸው እርሳቸው እንደ መምህር የተከተሉትን መንገድ ተማሪዎቻቸው በመከተላቸው መኮነን ይገባቸዋልን?

አንድ ሁላችንም የሚያግባባን ሀቅ በሀገራችን ከፍተኛው የሊግ እርከን በቋሚነት የክለባቸውን ግብ የሚጠብቁ ኢትዮጵያዊያን ግብ ጠባቂዎችን ፈልጎ ማግኘት ከባድ ሆኗል ፤ በዚህ ሂደት ውስጥ እጅግ ጥቂት ከሆኑ አሰልጣኞች በቀር አሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌን ጨምሮ አንዱ ሌላውን ለመውቀስ የሚያበቃ ሞራላዊ ሆነ አመክንዮአዊ ምክንያት ያለው የለም።በመሆኑም እግር ኳሳችን ለዘመናት ተጉዞበት ውጤት ካላስገኘለት የመወቃቀስ አባዜ ወጥተን መራራውን እውነታ በመጋፈጥ ለመፍትሔ መታተሩ ይበጃል እንላለን።