ዋልያዎቹ የመጨረሻ ስብስባቸውን ይዘው በሀዋሳ ከተማ ዝግጅታቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን መስከረም 13 ከሱዳን እንዲሁም መስከረም 19 ከሴኔጋል ጋር ለሚያደርጋቸው የ2027 አፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታዎች ዝግጅቱን ከጀመረ ሰነባብቷል።
የዋልያዎቹ አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ሀገርን ወክለው በአፍሪካ መድረክ እየተሳተፉ የነበሩት የሲዳማ ቡና እና የወልዋሎ ዓ/ዩ ጨዋታዎችን ለመታደም እንዲሁም ትናንት በተካሄደው 18ኛ መደበኛ የምርጫ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በመገኘታቸው ያለፉትን አምስት ቀናት ብሔራዊ ቡድኑን ልምምድ ሳያሰሩ መቆየታቸው ይታወሳል። አሰልጣኙ ዛሬ ቡድኑን የተቀላቀሉ ሲሆን በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሜዳ ልምምድ ማሰራታቸውም ታውቋል።
በዛሬው ልምምድ አዲስ የተጠሩት የወልዋሎ ተጫዋቾች በረከት ሳሙኤል እና ካርሎስ ዳምጠውን ጨምሮ አምስት የሲዳማ ቡና ተጫዋቾች ብሔራዊ ቡድኑ ተቀላቅለው ልምምዳቸውን ሰርተዋል። 23 ተጫዋቾችን የያዘው ብሔራዊ ቡድኑ ወደ መጨረሻው ምዕራፍ ዝግጅቱ የገባ ሲሆን ከቀናት በኋላ የሀዋሳ ከተማ ቆይታውን አጠናቆ ወደ መዲናዋ የሚመለስ መሆኑም ታውቋል።

