አሁን ጨዋታውን በሚያደርገው ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ስብስብ ውስጥ ቀድሞ መሰራት ያለበት ጉዳይ ባለማለቁ ምክንያት ሦስት ተጫዋቾች ከጨዋታው ውጭ መሆናቸውን አረጋግጠናል።

የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከደቂቃዎች በኋላ ከሞሮኮ ጋር ለሚያደርገው ከ23 ዓመት በታች አፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ከሰሞኑን እያደረጉ የሚገኙትን ዝግጅት ሶከር ኢትዮጵያ በቦታው በመገኘት መረጃዎችን ወደ እናንተ ስታደርስ መቆየቷ ይታወሳል።
ዛሬ ጨዋታው በሚደረግበት ሰዓት ሦስት ተጫዋቾች ቀድሞ መሰራት ያለበት ጉዳይ ባለማለቁ ምክንያት ከጨዋታው ውጭ መሆናቸውን አውቀናል።
ከጨዋታው ውጭ የሆኑት ተጫዋቾቹ ፉአድ ኢብራሂ ፣ ፀጋአብ ግዛው እና ገለታ ሀይሉ መሆናቸውን አውቀናል። ምክንያቱን ለማወቅ የምናደርገው ጥረት እንደተጠበቀ ሆኖ የፓስፖርታቸው ጉዳይ ዕድሜው አልፏል በሚል እንደሆነ ሰምተናል። በእነርሱ ምትክም ትናት ማታ ጥሪ የተደረገላቸው የድሬደዋ ከነማው ተከላካይ ሚኪያስ ካሳሁን እና የኢትዮጵያ ቡናው ተከላካይ ድልአዲስ ገብሬ መተካታቸውን አውቀናል። ድል አዲስ ገብሬ ለቀናት ከቡድኑ ጋር ያልነበረ ሲሆን አሁን በመጀመርያው አሰላለፍ እንዲካተት ሆኗል።
ሦስቱ ተጫዋቾች ላለፉት ቀናት ከቡድኑ ጋር ሲዘጋጁ ቆይተው ለጨዋታው እራሳቸውን እያዘጋጁ ባለበት ወቅት ትናት ማታ በድንገት ለጨዋታው ብቁ የሚያደርጋቹሁ ሰነድ አልተሟላም በማለት እንደማይጫወቱ መነገሩ ተጫዋቾቹ ስሜታቸው እንደተጎዳ ነግረውናል።
ሶከር ኢትዮጵያ በዚህ ጉዳይ ላይ በቀጣይ ተጨማሪ መረጃዎችን የምታደርስ ይሆናል።

