ኮትዲቯር ለአመታት ስትናፍቀው የነበረውን የአፍሪካ ዋንጫ በ2015 ኤኳቶሪያል ጊኒ ባስተናገደቸው የአፍሪካ ዋንጫ ማሳካት ችላለች፡፡
በፈረንጆቹ ሚሊንየም ወዲህ ካሜሮንን እና ግብፅ በተከታታይ ዋንጫውን ማንሳት የቻሉ ሃገራት ሲሆን ከ2010 ወዲህ አንድም ሃገር ይህንን ታሪክ መድገም አልቻለም፡፡ ኮትዲቯር የ2015 ክብሯን ለማስጠበቅ ከወዲሁ ፈታኝ ምድብ ይጠብቃታል፡፡ ዳግም አሸናፊ ለመሆን ከሚጠበቁ ሃገራት መካከል ብትኖርም በ2015 የነበሩ ከዋክብቶቿ አሁን ላይ አለመኖራቸው ትልቅ ስጋት ነው፡፡ በዛው ልክም ጥሩ ብቃት ያላቸው አዲስ ተጫዋቾችም ብቅ ማለታቸው ለዝሆኖቹ መልካም ነገር ነው፡፡
የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ብዛት፡ 21
ውጤት፡ ሁለት ግዜ አፍሪካ ቻምፒዮን (1992 እና 2015)
አሰልጣኝ፡ ሚሼል ዱሰየር
ኮትቯር በምድብ ሶስት ከዲ.ሪ. ኮንጎ፣ ቶጎ እና ሞሮኮ ጋር ተመድባለች፡፡ ኮትዲቯር በ2015 አፍሪካ ቻምፒዮን ከሆነች በኃላ አሰልጣኝ ሄርቬ ሬራርድ ከሃላፊነታቸው ስለለቀቁ የቀድሞ የቤኒን እና ጊኒ አሰልጣኝ የነበሩትን ፈረንሳዊው አሰልጣኝ ሚሼል ዱሰየርን ቀጥራለች፡፡ ዱሰየር የተቀበሉት ቡድን የአፍሪካ ቻምፒዮን እንደመሆኑ ለማነሳሳት እና ካለበት ከፍታ እንዳይወርድ ስራ ይጠብቃቸው ነበር፡፡ የማጣሪያ ምድባቸው በሶስት ሃገራት መካከል በሚደረግ ጨዋታ ብቻ መገደቡ እና ቡድኑ ወጥነት ያለው ውጤት አለማሳየቱ በደጋፊዎች ባይወደድም በሬናርድ ጥላ ስር የነበረውን ቡድን ዳግም ውጤታማ ለማድረግ ዱሰየር ትዕግስትን ይፈልጋሉ፡፡
ተስፋ
ኮትዲቯር ታታሪ እና ጠንካራ ሰራተኛ የሆኑ ጥራት ያላቸው ተጫዋቾችን መያዟ አሁንም ለስኬት እንድትታጭ አስችሏታል፡፡ ይህ ታታሪነት ታዲያ በሁሉም የቡድኑ ስፍራዎች ላይ የሚንፀባረቅ ነው፡፡ በትልልቅ ጨዋታዎች ላይ የመፈተን እና ውጤት የማምጣት ልምድን የያዙ ተጫዋቾች በከፊል መኖራቸው ሌላው ጠንካራ ጎን ነው፡፡ በአጥቂ መስመሩ ላይ የጀርቪንሆ መጎዳት አሳሳቢ ቢሆንም የዌልፍሬድ ዘሃ መኖር የማጥቃት አማራጫቸውን ያሰፋዋል፡፡ ሰሬ ዴይን የመሰለ በሜዳ ላይ የመምራት ብቃቱ እና ለተከላካዮች የሚገባውን ሽፍን መስጠት መቻሉ ለዝሆኖቹ በጋቦን ቆይታቸውን ይጠቅማቸዋል፡፡ አዲስ ቡድኑን የተቀላቀሉት እንደ ቤይሊ፣ ካኖን፣ ኬሲ እና ኮዲጃ ያሉት ተጫዋቾች ብቃታቸውን እና ጥራታቸው ላቅ ያለ መሆኑ የኮትዲቯር ሌላው ተስፋ ነው፡፡
ስጋት
በምድብ ማጣሪያው ወቅት አስተናጋጇ ጋቦን ጋር በመደልደላቸው በትኩረት ጨዋታቸውን ሲያደርጉ የነበረው ከሴራሊዮን እና ሱዳን ጋር ብቻ ነው፡፡ ይህም ቡድኑ የሚገባውን ያህል ጠንካራ ፉክክር ያለው ጨዋታ እንዳያገኝ አድርጎታል፡፡ በአለም ዋንጫ ማጣሪያ ማሊን ከኃላ ተነስተው ቢያሸንፉም ከሞሮኮ ጋር ግን 0-0 ሲለያዩ ቡድኑ የመሃል ሜዳው ክፍተት ታይቶበታል፡፡ ሰፊ የሜዳ ክልል ሸፍነው መጫወት የሚችሉ እንደ ሰሬ ዴይ እና ኬሲ ያሉ ተጫዋችን ቢይዝም በተፈጥሮ ክህሎት ያለው ፈጣሪ አማካይ ግን በቡድኑ አለመያዛቸው ውጤታቸው ላይ ተፅእኖ እንዳያሳድር ይሰጋል፡፡ በማጥቃቱ ረገድ የልምድ ያላው ጀርቪንሆ በጉዳት ከቡድኑ መለየት የራሱ የሆነ አሉታዊ ጎን አለው፡፡
የሚጠበቁ ተጫዋቾች
የመስመር አጥቂ ሆኖ መሰለፍ የሚችለው ዌልፍሬድ ዘሃ ከወራት በፊት ነበር ለኮትዲቯር ለመጫወት የወሰነው፡፡ ዘሃ ከቡድኑ ጋር ለመላለመድ አለመቸገሩ የተነገረ ሲሆን በወዳጅነት ጨዋታ ግብ የሆኑ ኳሶች አመቻችቶ ከማቀበል አልፎ ዩጋንዳ ላይ አንድ ግብ አስቆጥሯል፡፡ ዘሃ በጥሩ ብቃት ላይ ከተገኘ ያለው ፍጥነት ጋር ተደምሮ ለተጋጣሚ ተከላካዮች ፈታና ይሆናል፡፡
ብልሹ ፀባይ እንዳለው የሚታማው የቀኝ መስመር ተከላካዩ ሰርጅ ኦሪየር ሌላው መታየት ያለበት ተጫዋች ነው፡፡ ኦሪየር ከቀኝ መስመር እየተነሳ ግቦችን ከማስቆጠሩ ባሻገር ወደ አደጋው ክልል የሚልካቸው ክሮሶች በጣም ጥሩ ናቸው፡፡ በጣሊያን የሚጫወተው ወጣቱ አማካይ ፍራንክ ኬሲ ለኮትዲቯር የመሃል ሜዳ ጥንካሬን ያላብሳል፡፡ ከሳጥን ሳጥን የሚጫወተው ታታሪው ኬሲ ለዝሆኖቹ ጥሩ ግልጋሎትን ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ማክ ግራድል፣ ኤሪክ ቤሊ፣ ሰሬ ዴይ፣ ሲልቪያን ጎቦሆ እና ጆናታን ኮዲጃ ሌሎች መታየት ያለባቸው ተጫዋቾች ናቸው፡፡
የማጣሪያ ጉዞ
ኮትዲቯር በምድብ 9 ከአዘጋጇ ጋቦን፣ ሱዳን እና ሴራሊዮን ጋር ነበር የተደለደለችው፡፡ ከጋቦን ጋር የተደረጉት ጨዋታዎች እንደየወዳጅነት ስለተቆጠሩ ምንም ነጥብ አልተያዘባቸውም ነበር (በ2019 የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጇ ካሜሮን የምታደርጋቸው የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎች ነጥብ እንደሚያዙ ካፍ ባሳለፍነው ሳምንት መግለፁ ይታወሳል)፡፡ ኮትዲቯር ታዲያ ካደረገቻቸው አራት ጨዋታዎች በሶስት አቻ ስትለያይ ሱዳንን አንድ ግዜ ማሸንፍ ችላለች፡፡ ምድቡን በበላይነት ስትጨርስ 6 ነጥብ ነበራት ሁለተኛ እና ሶስተኛ ሆኗ ያጠናቀቁት ሴራሊዮን እና ሱዳን 5 እና 4 ነበራቸው፡፡ ዝሆኖቹ ሶስት ግቦችን ሲያስቆጥሩ ሁለት ግቦችን አስተናግደዋል፡፡
ሙሉ ስብስብ
ግብ ጠባቂዎች
ሳዮባ ማንዴ (ስታቤክ/ኖረዌይ)፣ ሲልቪያን ጎቦሆ (ቲፒ ማዜምቤ/ዲ.ሪ.ኮንጎ)፣ አሊ ባድራ (ኤኤስ ታንዳ/ኮትዲቯር)
ተከላካዮች
ኮኔ ላሚን (ሰንደርላንድ/እንግሊዝ)፣ ሰርጅ ካኖን (አዶ ላ ሓይ/ኔዘርላንድስ)፣ ሰርጅ ኦሪየር (ፒኤስጂ/ፈረንሳይ)፣ አዳማ ትራኦሬ (ኤፍሲ ቤል/ስዊዘርላንድ)፣ ሳይመን ዴሊ (ስላቪያ ፕራግ/ቼክ ሪፐብሊክ)፣ ኤሪክ ቤሊ (ማንችስተር ዩናይትድ/እንግሊዝ)፣ ማማዱ ባጋዮኮ (ሴንት ትሮንድ/ቤልጂየም)
አማካዮች
ሰርጅ ንጉሳን (ናንሲ ሎሬን/ፈረንሳይ)፣ ዣን ሚሼል ሴሪ (ኒስ/ፈረንሳይ)፣ ቢካንቲ አንግባን (ግራናዳ/ስፔን)፣ ቼክ ዶኮሬ (ሜትዝ/ፈረንሳይ)፣ ፍራንክ ኬሲ (አታላንታ በርጋሞ/ጣሊያን)፣ ሰሬ ዴይ (ኤፍሲ ቤል/ስዊዘርላንድ)
አጥቂዎች
ኒኮላስ ፔፔ (አንገርስ/ፈረንሳይ)፣ ሰሎሞን ካሉ (ኸርታ በርሊን/ጀርመን)፣ ዊልፍሬድ ዘሃ (ክርሰታል ፓላስ/እንግሊዝ)፣ ዊልፍሬድ ቦኒ (ስቶክ ሲቲ/እንግሊዝ)፣ ጂኦቫኒ ሲያዎ (ስታደ ሬን/ፈረንሳይ)፣ ጆናታን ኮዲጃ(አስቶንቪላ/እንግሊዝ)፣ ማክስ ግራድል (በርንማውዝ/እንግሊዝ)
ኮትዲቯር የአፍሪካ ዋንጫ ጉዞዋን ዛሬ ምሽት 1፡00 ላይ ቶጎን በስታደ ኦየም በመግጠም ትጀምራለች፡፡