የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ለ2016 የካሜሩን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ከአልጄርያ ብሄራዊ ቡድን ጋር ለሚያደርገው ጨዋታ ዛሬ ምሽት ወደ ስፍራው ያቀናል፡፡
ብሄራዊ ቡድኑ በመጀመርያው ምርጫ 30 ተጫዋቾችን በመያዝ በሱሉልታ ልምምድ ሲያደርግ የቆየ ሲሆን ካለፈው ሳምንት ጀምሮ 25 ተጫዋቾችን በመያዝ በአዲስ አበባ ስታድየም ዝግጅቱን ቀጥሏል፡፡ ዛሬ ጠዋት ደግሞ ወደ አልጀርስ የሚያቀኑ 20 ተጫዋቾችን በመያዝ ልምምድ አድርጓል፡፡ በዛሬው ልምምድ ላይ አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው እና ረዳቶቹ የመከላከል አጨዋወት እና የቆመ ኳስ አጠቃቀምን ሲያለማምዱ ታይታዋል፡፡
ከብሄራዊ ቡድኑ የ25 ተጫዋቾች ስብስብ መካከል የደደቢቷ ተከላካይ ውባለም ጸጋዬ በጉዳት ምክንያት ከቡድኑ ውጭ ሆናለች፡፡ ውባለም በልምምድ ላይ በደረሰባት ጉዳት ምክንያት ያለፉትን ቀናት ከቡድኑ ጋር ተቀላቅላ ልምምድ አልሰራችም፡፡ ውባለም ምናልባትም በመልሱ ጨዋታ ከጉዳቷ ሙሉ ለሙሉ አገግማ ወደ ቡድኑ ትመለሳለች ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የሲዳማ ቡናዋ አማካይ የካቲት መንግስቱ ፣ የጥሩነሽ ዲባባዋ ትደግ ፍስሃ ፣ የዳሽን ቢራዋ ሄለን እሸቱ እና የድሬዳዋ ከተማዋ ግብ ጠባቂ ታሪኳ በርገና ሌሎች ወደ አልጀርስ ከሚጓዘው ስብስብ የተቀነሱ ተጫዋቾች ናቸው፡፡ የጉዞው የቀሩት 5 ተጫዋቾች በሆቴል የሚቆዩ ሲሆን ቡድኑ ከአልጀርስ ከተመለሰ በኋላ ከቡድኑ ጋር በድጋሚ ይቀላቀላሉ፡፡
ብሄራዊ ቡድኑ 20 ተጫዋቾችን ጨምሮ የአሰልጣኞች ፣ የህክምና ባለሙያዎች ፣ የቡድን መሪ እና ጋዜጠኛን ያካተተ 26 የልኡካን ቡድን ይዞ ምሽት 4፡00 ላይ ወደ አልጀርስ ይበራል፡፡
ወደ አልጀርስ የሚጓዙት ተጫዋቾች የሚከተሉት ናቸው፡-
ግብ ጠባቂዎች
ዳግማዊት መኮንን – የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
ንግስት መዓዛ – የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
ተከላካዮች
መስከረም ኮንካ – ደደቢት
አሳቤ ሞሶ – ዳሽን ቢራ
ፋሲካ በቀለ – ዳሽን ቢራ
ፅዮን እስጢፋኖስ- የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
ጥሩነሽ መንገሻ – የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
እፀገነት ብዙነህ – የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
ሀብታም እሸቱ – የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
አማካዮች
ህይወት ደንጊሶ – የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
ቅድስት ቦጋለ – የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
ብሩክታዊት ግርማ – የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
ብርቱካን ገ/ክርስቶስ- ደደቢት
ኤደን ሽፈራው – ደደቢት
አዲስ ንጉሴ – ሀዋሳ ከተማ
እመቤት አዲሱ – መከላከያ
አጥቂዎች
ሽታዬ ሲሳይ – የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
ረሒማ ዘርጋ – የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
ሎዛ አበራ – ደደቢት
መዲና አወል – ቅድስተ ማሪያም
ሉሲዎቹ ከአልጄርያ ጋር የሚያደርጉት የመጀመርያ ጨዋታ በመጪው እሁድ አመሻሽ 12፡00 ላይ በአልጀርስ ይካሄዳል፡፡