የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 1ኛ ዙር (ቅዱስ ጊዮርጊስ እና መከላከያ በአፍሪካ ውድድሮች ምክንያት የተራዘሙ ጨዋታዎችን ሳይጨምር) በዚህ ሳምንት በሚደረጉ ጨዋታዎች ይጠናቀቃል፡፡ ዛሬ ሀዋሳ እና ይርጋለም ላይ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች የ13ኛው ሳምንት ጨዋታዎች የሚጀመሩ ሲሆን እሁድ እና ማክሰኞ ቀሪዎቹ 5 ጨዋታዎች ይደረጋሉ፡፡
ዛሬ በ09፡00 ሀዋሳ ላይ ሀዋሳ ከተማ ሊጉን ሁለት ተስተካካይ ጨዋታ እያለው የሚመራው ቅዱስ ጊዮርጊስን ያስተናግዳል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ተስፋዬ አለባቸውን አሁንም በጉዳት የማያሰልፍ ሲሆን በጉዳት ሲታመስ የከረመው ሀዋሳ ከተማ ተጫዋቾቹ በሙሉ ጤንነት ላይ መገኘታቸው መልካም ዜና ቢሆንም ወሳኞቹ ተጫዋቾች ታፈሰ ሰለሞን እና ጋዲሳ መብራቴ በዲሲፕሊን ጉዳይ በክለቡ መታገዳቸው ተሰምቷል፡፡ በዛሬው ጨዋታም አይሰለፉም ተብሏል፡፡
ሊጉን ከአዳማ በግብ ልዩነት በልጦ እየመራ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከተከታዮቹ በነጥብ ለመራቅ ፣ ሀዋሳ ከተማም ወደ ወራጅ ቀጠናው የመመለስ ስጋቱን ለመቅረፍ ወደ ሜዳ የሚገቡበት ጨዋታ በመሆኑ ጠንካራ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ይርጋለም ላይ ሰዳማ ቡና ዳሽን ቢራን ያስተናግዳል፡፡ ከተከታታይ ድሎች በኋላ አቻ እና ሽንፈት ያስተናገደው ሲዳማ ቡናን በሜዳው መርታት ፈታኝ ነው፡፡ ዘንድሮም ራሱን በወራጅ ቀጠና ያገኘው ዳሽን ቢራ ከሜዳው ውጪ ግብ ማስቆጠርና ነጥብ ይዞ መውጣት ፈተና ሆኖበታል፡፡ ከዳሽን ቢራ በኩል መድሃኔ ታደሰ ፣ ከሲዳማ ቡና በኩል በረከት አዲሱ በዚህ ጨዋታ አይሰለፉም፡፡ በ1990ዎቹ አስደናቂ የግብ ማግባት ሪኮርድ የነበራቸው ሁለቱ አጥቂዎች ከየክለባቸው አሰልጣኞች ጋር በዲሲፕሊን ጉዳይ ባለመስማማታቸው ከክለቡ ታግደዋል፡፡ ወሰኑ ማዜን በከባድ ጉዳት ያጣው ሲዳማ እንዳለ ከበደ ከጉዳት አገግሞ ለጨዋታው ብቁ ሆኖለታል፡፡
ሲዳማ ቡና በጨዋታው ወደ ድል ከተመለሰ ነጥቡን 21 በማድረስ ወደ ደረጃ ሰንጠረዡ አናት የሚጠጋ ሲሆን ዳሽን ቢራ የውድድር ዘመኑን 2ኛ የሜዳ ውጪ ድል ካስመዘገበ የወራጅ ቀጠናውን ለመከላከያ አስረክቦ 11ኛ ላይ ይቀመጣል፡፡
የ13ኛ ሳምንት ጨዋታዎች የሚከተሉት ናቸው፡-
አርብ የካቲት 25 ቀን 2008
09፡00 ሀዋሳ ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ (ሀዋሳ)
09፡00 ሲዳማ ቡና ከ ዳሽን ቢራ (ይርጋለም)
እሁድ የካቲት 27 ቀን 2008
09፡00 ድሬዳዋ ከተማ ከ አርባምንጭ ከተማ (ድሬዳዋ)
09፡00 ሀድያ ሆሳዕና ከ ደደቢት (ሆሳዕና)
ማክሰኞ የካቲት 29 ቀን 2008
09፡00 ወላይታ ድቻ ከ ኢትዮጵያ ቡና (ቦዲቲ)
09፡00 መከላከያ ከ አዳማ ከተማ (አአ ስታድየም)
11፡30 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ኤሌክትሪክ (አአ ስታድየም)
የደረጃ ሰንጠረዡ የሚከተለውን ይመስላል፡-
የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪዎች ደረጃ