ቻምፒዮንስ ሊግ ፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በመጀመርያው ጨዋታ በሜዳው አቻ ተለያየ 

በካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ 1ኛ ዙር የመጀመርያ ጨዋታ ባህርዳር ስታድየም ላይ ቲፒ ማዜምቤን ያስተናገደው ቅዱስ ጊዮርጊስ 2-2 አቻ ተለያይቷል፡፡

ፈጣን እና ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ የመድረስ እንቅስቃሴዎች በታዩበት የመጀመርያ አጋማሽ ቅዱስ ጉዮርጊስ በሃይሉ አሰፋ ባስቆጠረው እጅግ ድንቅ የ11ኛ ደቂቃ ጎል 1-0 መምራት ሲችል ከግቡ መቆጠር በኋላ እስከ 30ኛው ደቂቃ ድረስ በደጋፊው ድባብ ታግዞ ጥሩ እቅስቃሴ ማድረግ ችሏል፡፡ ቀስ በቀስ በመረጋጋት ወደ ጨዋታው መመለስ የቻሉት ቲፒ ማዜምቤዎች መደበኛው 45 ደቂቃ ተጠናቆ በጭማሪው 2 ደቂቃ መገባደጃ ላይ ዳንኤል አድጄይ ባስቆጠራት ግብ የመጀመርያውን አጋማሽ 1-1 አጠናቀዋል፡፡

የሁለተኛው አጋማሽ በተጀመረ ቅፅበት ቲፒ ማዜምቤዎች ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የግብ ክልል የላኩት ኳስ በአስቻለው ታመነ ተገጭታ ወደ ግብነት ተለውጣለች፡፡ ቁጥሩ ከፍተኛ የነበረው የባህርዳር ስታድየም ታዳሚን ድንጋጤ ውስጥ ቢከትም ቅዱስ ጊዮርጊሶች ጫና ፈጥረው በመጫወት በ59ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት ከተሻገረ ኳስ በአዳነ ግርማ ግብ አቻ መሆን ችለዋል፡፡ በቀሪው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ጫና ፈጥረው ለመጫወት ቢሞክሩም የማዜምቤን የተከላካይ መስመር እምብዛም ሳይፈትኑ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎችን ባስደሰተ መልኩ ጨዋታው 2-2 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡

IMG_5231

የክለቡ የበላይ ጠባቂ ሼክ መሃመድ ሁሴን አላሙዲ ፣ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ፣ የቲፒ ማዜምቤው ፕሬዝዳት ሞሰስ ካቱምቢ እና የብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ዮሃነስ ሳህሌን ጨምሮ በርካታ እንግዶች የተገኙ ሲሆን በግምት ከ50 እስከ 55 ሺህ የሚገመት ተመልካች ጨዋታውን ተከታትሏል፡፡ ጨዋታውም በመልካም የደጋፊዎች ድባብ ታግዞ ተጠናቋል፡፡

የሁለቱ ቡድኖች የመልስ ጨዋታ ከሳምንት በኋላ በኮንጎ ሉሙምባሺ ስታደ ቲፒ ማዜምቤ የሚካሄድ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስም በመጪው ሀሙስ ወደ ስፍራው ያቀናል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *