የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ለ2016 የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ማጣርያ ከአልጄርያ ጋር ለሚያደርገው የመልስ ጨዋታ በድጋሚ በመሰብሰብ ዝግጅት ማድረጉን ቀጥሏል፡፡
ብሄራዊ ቡድኑ ማክሰኞ ከአልጄርያ ከተመለሰ በኋላ ይዟቸው የተጓዛቸው 20 ተጫዋቾች እና ከጉዞው የቀሩት 4 ተጫዋቾች እንዲሁም አንድ አዲስ ተጫዋች በመቀላቀል ረቡእ እለት ቀላል ልምምድ ካደረገ በኋላ ሀሙስ ለተጫዋቾቹ እረፍት በመስጠት ከአርብ ጀምሮ መደበኛ ዝግጅቱን እያካሄደ ይገኛል፡፡
ቡድኑ በዛሬው እለት ጠዋት ሱሉልታ ልምምድ ያደረገ ሲሆን ከቀትር በኋላ ደግሞ በአዲስ አበባ ስታድየም ማጥቃት ላይ መሰረት ያደረገ ልምምድ ሰርቷል፡፡
ውባለም ጸጋዬ በጉዳት ከቡድኑ ውጭ በመሆኗ በብዙነሽ ሲሳይ ተተክታለች
ሉሲዎቹ ወደ አልጀርስ ከመብረራቸው በፊት እያደረጉ በነበረው ዝግጅት ጉዳት ያጋጠማት ተከላካይዋ ውባለም ጸጋዬ ከጉዳቷ ባለማገገሟ ከቡድኑ ውጭ ሆናለች፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንኳ ሁለገብ ተጫዋች ብዙነሽ ሲሳይ የደደቢቷን ተከላካይ ቦታ ተክታ ወደ ቡድኑ መቀላቀል ችላለች፡፡
አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው የወዳጅነት ጨዋታ እንደሚያገኙ ተስፋ አድርገዋል
ብሄራዊ ቡድኑ ከአልጄርያ ጋር ለሚያደርገው ጨዋታ ከ10 በላይ ቀናት የሚኖረው በመሆኑ የወዳጅነት ጨዋታ በማድረግ ለጨዋታው ለመዘጋጀት እያሰቡ እንደሆነ አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ከናይጄርያ ፣ ዚምባብዌ ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ታንዛንያ አንዳቸውን በዚህ ሳምንት መጨረሻ ለመግጠም ጥያቄ አቅርበናል፡፡ ከነዚህ ሃገራት በቅድሚያ የተቀበለንን ሃገር ለመግጠም እቅድ ይዘናል፡፡ ይህ ካልተሳካ ከዚህ ቀደም እዳረግነው ከተለያዩ የወንዶች ቡድኖች ጋር እንጫወታለን፡፡›› ብለዋል፡፡
ማጥቃት
በመጀመርያው ጨዋታ አልጀርስ ላይ የ1-0 ሽንፈት አስተናግደው የተመለሱት ሉሲዎቹ መጋቢት 17 ለሚደረገው የመልስ ጨዋታ ግቦች ማስቆጠር ላይ ማእከል ያደረገ ዝግጅት እንደሚያደርጉ ብርሃኑ ግዛው ተናግረዋል፡፡ ‹‹በሜዳችን የምናደርገው ጨዋታ በማሸነፍ ላይ ብቻ የተመሰረተ በመሆኑ ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ እንተገብራለን፡፡ በመጀመርያው ጨዋታ የአልጄርያን ጠንካራ እና ደካማ ጎን መመልከታችን ተጠቃሚ ያደርገናል›› ሲሉ አሰልጣኙ ተናግረዋል፡፡
የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ቅዳሜ መጋቢት 17 ቀን 2008 በአዲስ አበባ ስታድም እንዲካሄድ የተወሰነ ሲሆን ኢትዮጵያ ወደ ተከታዩ የማጣርያ ዙር ለማለፍ ግብ ሳይቆጠርባት 2 ግቦች ማስቆጠር ይጠበቅባታል፡፡