ኢትዮጵያ በአልጄርያ የ7-1 ከባድ ሽንፈት አስተናግዳለች

በአፍሪካ ዋንጫ የምድብ 10 ማጣርያ ብሊዳ ከተማ ላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን ያስተናገደው የአልጄርያ ብሄራዊ ቡድን 7-1 በሆነ ውጤት በመርታት የምድቡን መሪነት አጠናክሯል፡፡

ሙሉ ለሙሉ የጨዋታ ብልጫ የወሰደችው አልጄርያ መቁጠር የሚያዳግቱ በርካታ የግብ ሙከራዎችን እና የፍፁም ቅጣት ምት ብታመክንም በኢትዮጵያ መረብ ላይ 7 ግብ ከማስቆጠር አላገዳትም፡፡

የአልጄርያን ግቦች ሶፊያን ፌጉይሊ እና ኢስላም ስሊማኒ ሁለት ፣ የፍጹም ቅጣት ምት ያመከነው ያቺን ቤራሂሚ ፣ ተቀይሮ የገባው ረሺድ ጋዜል እና ሳፊር ታይደር አንድ አንድ አስቆጥረዋል፡፡ ከተቆጠሩት ግቦች የሳፊር ታይደር ግብ እጅግ አስገራሚ ነበረች፡፡ የቦሎኛው አማካይ ከሪያድ ማህሬዝ የተሻገረለትን የማእዘን ምት ኳስ ከፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውጪ በቀጥታ በቮሊ በመምታት አስቆጥሯል፡፡

የኢትዮጵያን ብቸኛ ግብ ከመረብ ያሳረፈው ጌታነህ ከበደ ነው፡፡ ጌታነህ ከራምኬል ሎክ የተሸገረለትን ኳስ ከአልጄርያ ተከላካዮች ራሱን ነፃ በማድረግ ከተቀበለ በኋላ በግብ ጠባቂው ሬይስ እግሮች መሃል አሾልኮ ከመረብ አሳርፏል፡፡

ድሉን ተከትሎ አልጄርያ ከ3 ጨዋታ ሙሉ 9 ነጥብ ይዛ ይድቡን መሪነት ስታሰፋ ኢትዮጵያ በ4 ነጥብ ትከተላለች፡፡ ነገ ጨዋታቸውን የሚያደርጉት ሲሸልስ እና ሌሶቶ በቅደም ተከተል በ1 እና 0 ነጥብ ተከታዩን ደረጃ ይዘዋል፡፡

ኢትዮጵያ እና አልጄርያ በ4ኛው የማጣርያ ጨዋታ በድጋሚ የሚገናኙ ሲሆን ማክሰኞ አዲስ አበባ ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡

ፎቶ – FootAfrica

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *