👉 “ፀጋዓብ ሦስት ዓመት ለሀዲያ ተጫዋቷል ሦስት ዓመት ይቀረዋል።” አቶ አባተ ተስፋዬ
👉 “ተመስገን ብርሃኑን በተመለከተም ሕግ ይከበር!” አቶ አባተ ተስፋዬ
👉 “እጄ ላይ ውሉ አለ ነፃ ተጫዋች በመሆኔ ወደ አሳዳጊዬ ክለብ ሄጃለሁ።” ፀጋዓብ ግዛው
👉 “ስድስት ዓመት አገልግዬ ሕጉን ተከትዬ ነው ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሄድኩት” ተመስገን ብርሃኑ
በፀጋአብ ግዛው እና በተመስገን ብርሃኑ ዝውውር ዙርያ እንዲሁም በሀዲያ በኩል ያለውን ሀሳብ ጭምር የሦስቱንም ወገኖች ምላሽ ሶከር ኢትዮጵያ እንዲህ አዘጋጅታለች።።

ከሰዓታት በፊት ሶከር ኢትዮጵያ ወጣቱ ሁለገብ ተጫዋች ፀጋአብ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ያደረገውን ዝውውር መዘገባችን ይታወሳል። ይህን ዘገባ ተከትሎ የሀዲያ ሆሳዕና ክለብ ሥራ አስኪያጅ አቶ አባተ ተስፋዬ “የፀጋአብ ዝውውር ላይ የሕግ ጥያቄ አለን” በማለት ተናግረዋል። ሶከር ኢትዮጵያም ተጫዋቾቹ ፀጋአብ ግዛው እና ተመስገን ብርሃኑ ጋር በመደወልና ያለውን ነገር በመጠየቅ የሦስቱንም አካል ሀሳብ ባካተተ መልኩ ተከታዩን ዘገባ አሰናድታለች።
አስቀድመን የአቶ አባተ ተስፋዬን ምላሽ እናስነብባችኋለን
ተጫዋቹ ፀጋአብ ተጨማሪ ቀሪ ውል አለው?
”ቀሪ ዓመት ማገልገል ግዴታ አለበት። አንደኛ በቢጫ ቲሴራ ሦስት ዓመት አገልግሏል፣ ሁለተኛ ደግሞ ”ወደ ዋናው ቡድን ማሳደግ ከፈለገ ሦስት ዓመት ማገልገል ግዴታ አለበት” የሚል ሕግ ነው ያለው፤ ያ ሕግ ይከበርልን።”
ስለዚህ ቀሪ ሦስት ዓመት የማገልገል ግዴታ አለበት?
”አዎ። አንቀጽ 18 የታዳጊ ወጣቶች ግዴታዎች የሚከተሉ ናቸው ይላል፤ ይሄንን ተከትሎ 18.1.4 ላይ የአስራ ስምንት እና ከዛ በላይ ሆኖ በውድድር እንዲሳተፍ ያሳደገው ክለብ ከመረጠው ሦስት ዓመት የመጫወት ግዴታ አለበት ይላል፤ ይሄ ሕግ ይከበርልን ነው።”
ተጫዋቹ ሀዲያ ሆሳዕና ቤት ስንት ዓመት አገልግሏል?
”በቢጫ ወጣቶች ቡድን ውስጥ ሦስት ዓመት አገልግሏል።”
ሲፈርም ፕሮፌሽናል ውል አይደለም የፈረመው? ከሆነ በቢጫ ነው ወይ በአረንጓዴ ነው የፈረመው?
”በቢጫ ነው የፈረመው።”
ስለዚህ ተጫዋቹ በሀዲያ ቤት ሦስት ዓመት የመቆየት ግዴታ አለበት ሌላ የትም መሄድ አይችልም?
”አዎ ሕጉ እንደዛ ነው የሚለው። በዛ ሕግ መሠረት ሕጉ ይከበርልን።”
ክለቡ ያስገባው ደብዳቤ ወይንም ከተጫዋቹ ጋር ያወራችሁት ነገር አለ?
”ከተጫዋቹ ጋር እንግዲህ በዚህ ሕግ ዙሪያ በደንብ አድርገን ነግረናል። አምናም አስገብተናል፤ ኢቭን አንድ ተጫዋች በዚህ ልክ ጥሎ ሄዶ ነበር ምናልባት የምታስታወሱ ከሆነ ያሬድ በቀለ የሚባል ተጫዋች ሸገር ከተማ ሄዶ ገብቶ ነበር በዚህ ሕግ ነው ከሰን የመለስነው፤ እነሱንም ጭምር ሌሎችም የመሄድ አዝማሚያ ሲያሳዩ አምናም የክስ ደብዳቤ አስገብተናል። ምናልባት እነዚህ ተጫዋቾች የኛ ንብረት ስለሆኑ እኛ ስለምንፈልጋቸው መጥተው እንዳይፈርሙ የሚል ነገር አስገብተን ያሬድ በቀለን በዛ ሕግ መሠረት መልሰናል። አሁንም ለዚህ ተጫዋች ሕጉ ይከበርልን የሚል ጥያቄ ነው ያቀረብነው።”
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ተመስገን ተመሳሳይ ዓይነት ጉዳይ ያለው ይመስለናል፤ የእርሱ ዝውውር እንዴት ነው? እሱ ላይሳ ምን አስተያየት አላችሁ?
”ተመሳሳይ ነው። ተመስገን ሁለት ዓመት አገልግሏል በአረንጓዴ አንድ ዓመት ይቀረዋል፤ ያንንም አብሮ ነው ክሱን የምናስገባው ተመስገን ብርሃኑ ቲሙን የማገልገል አንድ ዓመት ግዴታ ስላለበት እሱንም ሕግ የማስከበር ስራ ነው የምንሰራው።”
ለፌዴሬሽኑ ያስገባችሁት ደብዳቤ አለ?
”አሁን ነው የምናስገባው። አሁን ጠቅለል አድርገን ልናስገባ ነው።”

