የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን አፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ማጣርያ ወደ ተከታዩ ዙር ለማለፍ ዛሬ ከአልጄርያ ብሄራዊ ቡድን ጋር የመልስ ጨዋታውን ያደርጋል፡፡
የሉሲዎቹ የተከላካይ መስመር ተጫዋች ፅዮን እስጢፋኖስ ከአልጀርስ የሚፈልጉትን ውጤት ይዘው እንደተመለሱ ገልፃ አልጄርያን እንደጠበቁት ከባድ ተጋጣሚ እንዳልሆነ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረገችው ቆይታ ተናግራለች፡፡
‹‹ ከሞላ ጎደል ከአልጀርሱ ጨዋታ የምንፈልገውን አሳክተን ተመልሰናል ብለን እናስባለን፡፡ ነጥብ ይዘን አልያም በጠባብ የግብ ልዩነት ተሸንፈን መምጣት ነበር አላማችን፡፡ አልጄርያን እንደ ስሟ እና በሜዳዋ እንደመጫወቷ ለነሱ ትልቅ ግምት ሰጥተን ነበር ወደ ሜዳ የገባነው፡፡ በአንፃሩ አልጄርያዎች ደግሞ እኛን እንደቀላል ተጋጣሚ ተመልክተውን ነበር፡፡ ለኛ ትንሽ ግምት ቢሰጡንም ጥሩ መንቀሳቀስ ችለን ነበር፡፡ ጨዋታው ላይ ጠንከር ያለ የቡድን ስራ ነበረን፡፡ ከነበረኝ ግምት ይሁን ፣ ከወንዱ ብሄራዊ ቡድን ዝና ይሁን ፣ እኛ የተሻለ መንቀሳቀስ ስለቻልን ይሁን አላውቅም እንደጠቅኳቸው ጠንካሮች አይደሉም፡፡ ››
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ወደ ተከታዩ ዙር ለማለፍ ግቦች ማስቆጠር እና ግብ ሳያስተናግድ መውጣት ይጠበቅበታል፡፡ ቡድኑ ለመልሱ ጨዋታ በነበረው ዝግጅትም ማጣቃት ላይ ያተኮረ ልምምድ ሲሰራ በተደጋጋሚ ተስተውሏል፡፡ ነገር ግን ፅዮን ማጥቃት ላይ ብናተኩርም መከላከሉን አልዘነጋነውም ትላለች፡፡
‹‹ ቅድም እንዳልኩት በአልጀርሱ ጨዋታ ጠንካራ የቡድን ስራ ነበረን፡፡ በአልጀርስ ስንከላከል ማጥቃቱን እንዳልረሳነው ሁሉ ዛሬ ሙሉ ሉሙሉ ለማጥቃት ብንገባም የመከላከል ስራውን መዘንጋት የለብንም፡፡ እኔ በግሌ አጋጣሚዎችን በመጠቀም ለማጥቃት ከመሞከር ባሻገር ስራዬ መከላከል እስከሆነ ድረስ ዋነኛ ስራዬ የሚሆነው መከላከል ነው፡፡ እዚህ ለመልሱ ጨዋታ ስንዘጋጅም መከላከሉን የዘነጋነው አይመስለንም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የአራታችን ተከላካዮች ጥምረት ጠንካራ ነው፡፡›› ብላለች፡፡
በአልጀርስ ጥሩ እንቅስቃሴ ያደረገችው ፅዮን በመጨረሻም በብዙ ጥረት የተገኘውን እድ ለመጠቀም እንደተዘጋጁና በእርግጠኝነት ወደ ተከታዩ ዙር እንደሚያልፉ ገልፃለች፡፡
‹‹ሁላችንም ጨዋውን ለማሸነፍ በጥሩ ሞራል ላይ እንኛለን፡፡ ወደ አፍሪካ ዋንጫው የተመለስንበትን መንገድም ሁላችንም እንደምናውቀው ስለነበር አሸንፈን ማለፉን እፈልገዋለን፡፡ በዛሬው ጨዋታ በሙሉ እርግጠኝነት የምናልፍ ነው የሚመስለኝ፡፡ ››