የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ማጣር ወደ ተከታዩ ዙር ለማለፍ የአልጄርያ ብሄራዊ ቡድንን አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ያስተናግዳል፡፡ በዛሬው የመልስ ጨዋታ ዙርያ ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየቷን የሰጠችው ግብ ጠባቂዋ ዳግማዊት መኮንን በስብስባቸው ውስጥ ያለውን ልምድ በመለዋወጥ ለዛሬው ጨዋታ እንደተዘጋጁ ተናግራለች፡፡
‹‹ ከችሎታ በዘለለ ለአንድ ተጫዋች የሚያስፈልገው ልምድ ነው፡፡ በስብስባችን ውስጥ እያንዳንዳችን በብሄራዊ ቡድን እና በክለብ ውድድሮች የየራሳችን ልምድ አለን፡፡ ከእኔ በላይ በብሄራዊ ቡድን በመጫወት የበለጠ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾችም አሉ ፤ ከ20 አመት በታች ባለው ቡድን የነበሩ ተጫዋቾችም የኢንተርናሽናል ጨዋታ ልምድ አካብተዋል፡፡ ያንን ልምድ እየተለዋወጥን ጥሩ ዝግጅት አድርገናል፡፡ ›› ትላለች፡፡ ዳግማዊት አክላም በአልጀርስ ጨዋታ ከአልጄርያ ይልቅ ቅዝቃዜው ፈተና ሆኖባቸው እንደነበር ትገልጻለች፡፡
‹‹ ጨዋታው ብዙ ፈታኝ አልነበረም፡፡ ለኛ አስቸጋሪ የነበረው ቅዝቃዜው ነበር፡፡ ምክንት ማቅረብ እንዳይሆን እንጂ ቅዝቃዜ ሲኖር ራስህን አውጥተህ ለመጫወት ሰውነትን ይገታዋል፡፡ በዚህም ምክንያት እንደፈለግን መጫወት አልቻልንም እንጂ ጥሩ ተንቀሳቀስናል፡፡ ››
ዳግማዊት ከአልጄርያ ብሄራዊ ቡድንን ከቪድዮ ባሻገር በሜዳ ላይ መመልከታቸው ጥንካሬ እና ድክመታቸውን በመለየት ለዛሬው ጨዋታ እንዲዘጋጁ እንዳደረጋቸው ተናግራለች፡፡ ‹‹ከዚህ በፊት አልጄርያን የምናውቃቸው በአፍሪካ ዋንጫ ያደረጉትን እንቅስቃሴ በቪድዮ በመመልከት ነበር፡፡ አሁን ደግሞ በቪድዮ ከሚታየው በዘለለ 90 ደቂቃ ስለተጫወትን በደንብ አውቀናቸዋል፡፡ የቱ ጋር ጠንካራ እንደሆኑ ፣ የቱ ጋር ደካማ እንደሆኑ የቱ ጋር ክፍተት እንደምናገን አውቀናል፡፡ በምን አይነት ሁኔታ ብንሄድ እናሸንፋለን ብለን በመነጋገር ጥሩ ተዘጋጅተናል ብለን እናስባለን፡፡››
በውድድር ዘመኑ በጉዳት ምክንያት ጨዋታዎች ማድረግ ያልቻለችው ዳግማዊት ለብሄራዊ ቡድን መመረጥ ብዙዎች ትያቄ ቢያነሱበትም ከጉዳታሙሉ ለሙሉ በማገገሟና ብቁነቷ ስለታመነባት እንደተመረጠች ትናገራለች፡፡
‹‹ በዚህ የውድድር ዘመን ብዙ ጨዋታ ያልተጫወትኩት በጉልበት ጉዳት ምክንያት ነው፡፡ ከዛ አንጻር ብዙ ጨዋታ ማድረግ አልቻልኩም፡፡ አሁን ደግሞ ለጨዋታ ብቁ ናት ተብዬ ስመረጥ ሃላፊነቴን መወጣት ነው ከእኔ የሚጠበቀው፡፡
‹‹ከጉዳት መመለሴ በጨዋታው ላይ ተጽእኖ አልፈጠረብኝም፡፡ ነገር ግን ቅዝቃዜው እንደልብ እንድቆም ሲያደርገኝ አልነበረም፡፡ የጉልበት ጉዳት ቅዝቃዜ ካገኘው እንደፈለግክ እንድትሆን አያደርግህም፡፡ በዛ ጨዋታ የህክምና ባለሙያዎች እርዳታ እንዲያደርጉ ያደረግኩት ከቅዝቃዜው የመጣ እንጂ ሳላገግም ቀርቼ አይደለም፡፡ በውድድር አመቱ ጨዋታ አለማድረጌም በጨዋታው ላይ ምንም አይነት ተፅእኖ አልፈጠረብኝም፡፡ ›› ትላለች፡፡
ዳግማዊት በንግድ ባንክም ሆነ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በተደጋጋሚ የፍፁም ቅጣት ምት በማዳን ችሎታዋ ትታወቃለች፡፡ የዛሬው ጨዋታ ወደ ፍጹም ቅጣት ምት ካመራ ዳግማዊት ብሄራዊ ቡኑን ወደ ድል ትመራው ይሆን? ዳግማዊት መልስ አላት
‹‹ አጥቂዎቻችን የመለያ ፍጹም ቅጣት ምት ደረጃ እንድንደርስ የሚያደርጉ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ከመቼውም ጊዜ በላይ ምርጥ አጥቂዎችን ይዘናል፡፡ ሽታዬ ፣ ረሂማ እና ከሁሉም በላይ ደግሞ ከ20 አመት በታች ቡድን ላይ ታሪክ የሰራችው ሎዛ አበራ ባሉበት ወደ መለያ ፍፁም ቅጣት ምት እንደርሳለን ብዬ አላስብም፡፡ ነገር ግን በጨዋታው የሚፈጠረው ስለማይታወቅ ወደ መለያ ምት ልናመራ እንችላለን፡፡ በክለቤ ንግድ ባንክ ለ3 አመታት መለያ ፍጹም ቅጣት ምቶችን በማዳን ቻምፒን እንዲሆን ረድቻለሁ፡፡ ስለዚህ ወደ ፍፁም ቅጣት ምት ካመራን ባለኝ ልምድ ተጠቅሜ ለቡድኔ የተሸለ ነገር አበረክታለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡ ››
የንግድ ባንኳ ግብ ጠባቂ በመጨረሻም ጨዋታውን እንደሚያሸንፉ በመተማመን ተናግራለች፡፡ ‹‹ እኔ የሚታየኝ በእርግጠኝነት እንደምናሸንፍ ነው፡፡እንደውም እያሰብኩት ያለሁት በቀጣዩ ዙር ስለምንገጥመው የኬንው ብሄራዊ ቡድን ነው፡፡ ይህን ስል ግን የዛሬውን ጨዋታ ትኩረት አልሰጠነውም ማለት አይደለም፡፡ ››