ጋቦን 2017፡ በትላንት ጨዋታዎች ካሜሮን ከደቡብ አፍሪካ አቻ ሲለያዩ ሴኔጋል ለማለፍ ያቃረባትን ድል አስመዝግባለች

የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎች ቅዳሜም ቀጥለው ተደርገዋል፡፡ ያውንዴ ላይ ካሜሮን ከደቡብ አፍሪካ 2-2 ሲለያዩ ዩጋንዳ በቡርኪና ፋሶ ኡጋዱጉ ላይ ሽንፈት አስተናግዳለች፡፡ ዲ.ሪ. ኮንጎ አንጎላን ኪንሻሳ ላይ አሸንፋለች፡፡

ኢትዮጵያዊው የመሃል ዳኛ ባምላክ ተሰማ በመራው ጨዋታ ካሜሮን ከደቡብ አፍሪካ በአቻ ውጤት ጨዋታቸውን አጠናቅቀዋል፡፡ ቶኬሎ ራንቴ እና ሆሎምፖ ኬካና ለባፋና ባፋና ስያስቆጥሩ ሰባስቲየን ሲያኒ እና ኒኮላስ ኑኮሎ ለማይበገሩት አናብስት ግቦቹን አስቆጥረዋል፡፡ ኬካና ያስቆጠራት ግብ ከደቡብ አፍሪካ የሜዳ ክልል በመሆኑ ብዙዎች አድናቆታቸውን ችረውታል፡፡

ምድብ 13ን ካሜሮን በ7 ነጥብ ስትመራ ሞሪታንያ በ6 ትከተላለች፡፡ ከሶስት ጨዋታዎች 2 ነጥብ ብቻ የሰበሰበችው ደቡብ አፍሪካ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡

ዩጋንዳ የምድብ 4ን መሪነት በቡርኪና ፋሶ አስረክባለች፡፡ ኦጋዱጉ ላይ በተደረገው ጨዋታ የቡርኪናን የድል ግብ ጆናታን ፔትሮፒያ በፍፁም ቅጣት ምት አስቆጥሯል፡፡ ምድቡን ቡርኪናፋሶ እና ዩጋንዳ በዕኩል ስድስት ነጥብ ይመሩታል፡፡ 

ሞሮኮ ከሜዳዋ ውጪ ኬፕ ቬርዴን 1-0 ስትረታ የሱፍ ኤል-አረቢ የጨዋታውን ብቸኛ ግብ በፍፁም ቅጣት ምት በመጀመሪያው አጋማሽ ከመረብ አሳርፏል፡፡ ምድብ 6ን ሞሮኮ በ9 ነጥብ ስትመራ ኬፕ ቬርዴ በ6 ትከተላለች፡፡ 

በምድብ 10 ከኢትዮጵያ ጋር የተደለደሉት ሲሸልስ እና ሌሴቶ ቪክቶሪያ ላይ ተገናኘተው ሲሸልስ 2-0 ማሸነፍ ችላለች፡፡ የሲሸልስን የድል ግብ የሴንት ሚሸሉ አጥቂ ጀርቫስ ዋይ-ሄይቭ እና ዲን ሱዜት በስማቸው አስመዝግበዋል፡፡

ድሉን ተከትሎ ሲሸልስ ነጥቧን ወደ አራት አሳድጋ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡ ሲሸልስ ከኢትዮጵያ የተሻለ የግብ ክፍ ቢኖራትም ካፍ ከግብ ክፍያ ይልቅ እርስ በርስ ተገናኘተው ለሚለው ህግ ቅድሚያ ይሰጣል፡፡

ቡሩንዲ ቡጁምቡራ ላይ ናሚቢያ 3-1 ተሸንፋለች፡፡ ለናሚቢያ ፒተር ሳሉሊሌ፣ ቤንሰን ሲሎንጎ እና ሄንድሪክ ሶማብ ሲያስቆጥሩ ቡሩንዲን ከመሸነፍ ያላዳናች ግብ የብሄራዊ ቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች ፊስተን አብዱልራዛክ በስሙ አስመዝግቧል፡፡

ዳካር ላይ ሴኔጋል ኒጀርን 2-0 በማሸነፍ ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ተቃርባለች፡፡ የሳውዝሃምፕተኑ ሰይዶ ማኔ ኮከብ ሆኖ በዋለበት ጨዋታ ለቴራንጋ አንበሶቹ መሃመድ ዲያሜ እና ኦማር ኒያስ ኳስ እና መረብን አገናኝተዋል፡፡ ምድብ 11ን ሴኔጋል በ9 ነጥብ ትመራለች፡፡

ሩዋንዳ በሞሪሽየስ አስደንጋጭ ሽንፈት አስተናግዳለች፡፡ ፍራንሲስ ራሶሎፎኒሪና ያስቆጠራት ብቸኛ ግብ ለሞሪሽየስ ሶስት ነጥብ ለማስገኘት በቂ ነበረች፡፡ በምድብ 9 ሞሪሽየስ በስድስት ነጥብ ጋናን ተከትላ ሁለተኛ ነች፡፡

የቻን አሸናፊዋ ዲ.ሪ. ኮንጎ በሴድሪክ ባካምቡ እና ሚቻክ ኤሊያ ግቦች አንጎላን 2-1 አሸንፈዋል፡፡ ፍሬዲ ለአንጎላ በጭማሪ ሰዓት በፍፁም ቅጣት ምት አስቆጥሯል፡፡ ፍሬዲ ያስቆጠራት ፍፁም በ90+8ኛው ደቂቃ የተገኘች ሲሆን የመሃል ዳኛው የጨመሩት ደቂቃ አምስት ብቻ መሆኑ ብዙዎችን አስገርሟል፡፡ ኮንጎ የምድብ ሁለትን መሪነት ከአንጎላ ተረክባለች፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *