ጋቦን 2017፡ አራተኛ የምድብ ማጣርያ ጨዋታዎች ዛሬ ሲጀመሩ ኬኒያ በድጋሚ ተሸንፋለች 

የአፍሪካ ዋንጫ 4ኛ የምድብ ማጣርያ ጨዋታዎች ዛሬ ሲጀምሩ አላስፈላጊ የደጋፊዎች ስረዓት አልበኝበት በታየበት ጨዋታ ናይሮቢ ላይ ኬኒያ በጊኒ ቢሳው 1-0 ተሸንፋለች፡፡ ቦትስዋና ኮሞሮስን ፣ ቤኒን ደቡብ ሱዳንን ሲረቱ ጋና እና ዛምቢያ ነጥብ ጥለዋል፡፡

በናይሮቢው ናያዮ ስታዲየም በተረገ ጨዋታ ኬንያ በጊኒ ቢሳው 1-0 ተሸንፋ ለጋቦኑ የአፍሪካ ዋንጫ የማለፍ ተስፋዋን አጨልማለች፡፡ ማሸነፍን ብቻ አላማ አድርገው ወደ ሜዳ የገቡት የሃራምቤ ከዋክብቶቹ የጨዋታ የበላይነት የነበራቸው ቢሆንም የበላይነታቸውን ወደ ውጤት ሊለውጡት አልቻሉም፡፡ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ዘጠኝ ደቂቃዎች ሲቀሩት ሜንዴዝ ወሳኝን ግብ ለምዕራብ አፍሪካዊያኖቹ አስቆጥሯል፡፡ በግቧ መፅደቅ የበሸቁ የኬንያ ደጋፊዎችም ድንጋይ እና ጠርሙሶችን ወደ ሜዳ ሲወረውሩ ታይተዋል፡፡ ደጋፊዎቹ ከፖሊስ ጋርም የተጋጪ ሲሆን ጨዋታው ከ20 ደቂቃዎች በላይ ሊቋረጥ ችሏል፡፡

በዚህ ምድብ የሚገኙት ኮንጎ ብራዛቪል እና ዛምቢያ አሁንም አቻ ተለያይተዋል፡፡ ጃርዳን ማሳንጎ ባለሜዳዎቹን ቀዳሚ ሲያደርግ በዓመቱ መጀመሪያ የኮንጎውን ኤሲ ሊዮፓርድስን ተቀላቅሎ መልካም የውድድር ዘመን እያሳለፈ የሚገኘው ዊንስተን ካሌንጎ ቺፖሎፖሎዎቹን አቻ አድርጓል፡፡ ምድብ 5ን ጊኒ ቢሳው በ7 ነጥብ ስትመራ ኮንጎ ብራዛቪል እና ዛምቢያ በ6 ተከታዮቹን ደረጃዎች ይዘዋል፡፡

በምድብ 3 ቤኒን ኮትኑ ላይ ደቡብ ሱዳን በቤኒን 4-1 ተሸንፋለች፡፡ ለቤኒን የድል ግቦቹን ስቱፈን ሴሴኞ (ሁለት)፣ ሚካኤል ፖት እንዲሁም ጆደል ዶሶ ከመረብ አዋህደዋል፡፡ አታክ ሉአል ደቡብ ሱዳንን ከባዶ መሸነፍ ያደነች ግብ አስቆጥሯል፡፡ ምድቡን ቤኒን በ8 ነጥብ ስትመራ ማሊ በሰባት ትከተላለች፡፡

ጆይል ሞጎሮሲ አሁንም የቦትስዋና ወሳኝ ተጫዋች መሆኑን ባሳየበት ጨዋታ ዜብራዎቹ ኮሞሮስን 2-1 አሸንፈዋል፡፡ በማቻንጋማ የሱፍ ግብ የመሩት ኮሞሮሶች በሁለተኛው አጋማሽ በገባባቸው ሁለት ግቦች ተሸንፈው ወጥተዋል፡፡ ጋላብግዊ ሞያና እና ሞጎሮሲ ቦትስዋና ሶስት ነጥብ ይዛ እንድትወጣ የረዷት ተጫዋቾች ናቸው፡፡ በምድብ 4 ቦትስዋና፣ ዩጋንዳ እና ቡርኪና ፋሶ ዕኩል 6 ነጥብ አላቸው፡፡

ጋና ለአፍሪካ ዋንጫው ለማለፍ ከጫፍ ደርሳለች፡፡ ብላክ ስታርሶቹ ዛሬ ከሞዛምቢክ ጋር ያደረጉትን ጨዋታ ያለግብ አጠናቅቀዋል፡፡ ምድብ 8ን ጋና በ10 ነጥብ ስትመራ ሞሪሽየስ በ6 ትከተላለች፡፡

የዕሁድ ውጤቶች፡-

ቦትስዋና 2-1 ኮሞሮስ

ሞዛምቢክ 0-0 ጋና

ቤኒን 4-1 ደቡብ ሱዳን

ኬንያ 0-1 ጊኒ ቢሳው

ኮንጎ ብራዛቪል 1-1 ዛምቢያ

የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎቹ ሰኞም ቀጥለው ይደረጋሉ፡፡ ዳሬሰላም ላይ ታንዛያን ልትገጥም የነበረቸው ቻድ እሯሷን ከማጣሪያው በማግለሏ ጨዋታው አይካሄድም፡፡ በምድብ 7 ከግብፅ ታንዛኒያ እና ናይጄሪያ ጋር ተደልድላ የነበረቸው ማዕከላዊ አፍሪካዊቷ ሃገር ቻድ በፋይናንስ እጥረት ምክንያት ከማጣሪያው ውጪ መሆኗን አሳውቃለች፡፡

ካፍ የቻድ እግርኳስ ማህበርን 20ሺ የአሜሪካ ዶላር የቀጣ ሲሆን ከወዲሁም ካሜሮን በምታዘጋጀው የ2019 የአፍሪካ ዋንጫም ውጪ አድጓል፡፡ በምድቡ ላይ የነበሩ የቻድ ውጤቶችም በሙሉ ተሰረዝዋል፡፡ በዚህም መሰረት ግብፅ እና ታንዛኒያ ኒጃሚና ላይ የነበራቸው የ5-1 እና የ1-0 እንዲሁም ናይጄሪያ በሜዳዋ 2-0 ቻድን ያሸነፉበት ውጤቶች ተሰርዘዋል፡፡ ግብፅ አሁንም ምድቡን በ4 ስትመራ፣ ናይጄሪያ በ2 ትከተላለች፡፡ ታንዛኒያ አንድ ነጥብ አላት፡፡

በስፔናዊው ሃቪየር ክሌሜንቴ የምትሰለጥነው ሊቢያ ሙሉ ለሙሉ ከአፍሪካ ዋንጫው ማጣሪያ ውጪ ላለመሆን ሳኦ ቶሜ እና ፕሪንስፔን ለማሸነፍ ወደ ሜዳ ትገባለች፡፡ ማሊ የምድብ 3 የበላይነትን ከቤኒን ለመረከብ ኤኳቶሪያል ጊኒን ማላቦ ላይ ትገጥማለች፡፡ ሐራሬ ላይ ዚምባቡዌ ከስዋዚላንድ የምድብ 12ን አናት ለመቆናጠጥ ይጫወታሉ፡፡

የሰኞ ጨዋታዎች፡-

18፡00 – ሊቢያ ከ ሳኦ ቶሜ እና ፕሪንስፔ (ፔትሮስፖርት ስታዲየም ካይሮ)

15፡00 – ማዕከላዊ አፍሪካ ከ ማዳስካር (ባንግዊ ስታዲየም)

15፡00 – ዚምባቡዌ ከ ስዋዚላንድ (ናሽናል ስፖርትስ ስታዲየም)

16፡30 – ሴራሊዮን ከ ጋቦን (ናሽናል ስታዲየም)

17፡00 – ኢኳቶሪያል ጊኒ ከ ማሊ (ኢስታዲዮ ዲ ማላቦ)

ፎቶ – ቦትስዋና ከ ኮሞሮስ (አፍሪካ ቶፕ ስፖርት)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *