የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሊግ የ2008 የውድድር ዘመን 1ኛው ዙር ትላንት ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡ በኢትዮጵያ የሊግ እርከን 3ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሊግ ከሁሉም ሊጎች ዘግይቶ ቢጀመርም የአንደኛውን ዙር ቀድሞ አጠናቋል፡፡ እኛም በብሄራዊ ሊጉ ዙርያ አንባብያን የጠራ መረጃ እንዲኖራቸው በማስብ ቡድኖች ወደ ከፍተኛ ሊግ የሚያድጉበትን ፣ ወደ ክልል ሊጎች የሚወርዱበትን አሰራር እንዲሁም ሌሎች ሊያውቋቸው የሚገቡ ጠቃሚ ነጥቦች እንመለከታለን፡፡
ወደ ከፍተኛ ሊጉ እንዴት ያልፋሉ?
-በተመረጠ ከተማ (የውድድሩ ቦታ እስካሁን አልተወሰነም) 16 ክለቦች የሚሳተፉበት የማጠቃለያ ውድድር ይካሄዳል፡፡ 6 ክለቦችም ወደ ከፍተናው ሊግ ያድጋሉ፡፡
-እነማን ያልፋሉ? በ7 ዞኖች በሚደረጉ የዙር ውድድሮች 1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ይዘው የሚያጠናቅቁ 14 ክለቦች በቀጥታ ወደ ማጠቃለያው ዙር ያልፋሉ፡፡ በጥሩ 3ኛነት የሚያጠናቅቁ 2 ክለቦች ወደ ማጠቃለያው ውድድር የማለፍ እድል ያገኛሉ፡፡
-ጥሩ 3ኛ እንዴት ይለያል? 3ኛ ደረጃ የሚያጠናቅቁ ክለቦች ያገኙት ነጥብ ላደረጉት ጨዋታ ተካፍሎ በሚገኘው አማካይ ነጥብ ከፍተኛ የሆነው ቡድን በጥሩ 3ኛነት ያልፋል፡፡
-የማጠቃለያ ውድድሩ በ4 ምድቦች ተከፍሎ የሚካሄድ ሲሆን ከምድብ አልፈው በሩብ ፍፃሜው 8 ክለቦች እርስ በእርስ በሚያደርጉት የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ወደ ግማሽ ፍጻሜ የሚያልፉት 4 ክለቦች በቀጥታ ወደ ከፍተኛ ሊግ ማለፋቸውን ያረጋግጣሉ፡፡ ተሸናፊዎቹ 4 ክለቦች ደግሞ እርስ በእርስ የመለያ (playoff) ጨዋታ አድርገው ሁለቱ አሸናፊ ክለቦች ወደ ከፍተኛ ሊግ ያልፋሉ፡፡
ወራጅ ክለቦችስ?
የየዞናቸውን የመጨረሻ ደረጃ ይዘው የሚያጠናቅቁ በአጠቃላይ 7 ክለቦች ከብሄራዊ ሊጉ ወርደው በየክልሎቻቸው ሊገች ይወዳደራሉ፡፡
በአጠቃላይ በሶስቱ የሊግ እርከኖች በአመቱ መጨረሻ እና በቀጣዩ አመት የሚኖረው ገጽታ ይህንን ይመስላል፡-
ፕሪሚየር ሊግ – 2 ክለቦች ወደ ከፍተኛ ሊግ ሲወርዱ 4 ክለቦች ከከፍተኛው ሊግ ያድጋሉ፡፡ በቀጣይ አመትም የፕሪሚየር ሊጉ ተሳታፊዎች ቁጥር 16 ይሆናል፡፡
ከፍተኛ ሊግ – 4 ክለቦች (ከየምድቡ 1ኛ እና 2ኛ የወጡ) ወደ ፕሪሚየር ሊግ ሲያድጉ 4 ክለቦች (ከየምድቡ 15ኛ እና 16ኛ የሚወጡ) ወደ ብሄራዊ ሊግ ይወርዳሉ፡፡ 6 ክለቦች ከብሄራዊ ሊግ ወደ ከፍተኛ ሊግ አድገው በቀጣዩ አመት በ32 ክለቦች መካከል ውድድሩ ይካሄዳል፡፡
ብሄራዊ ሊግ – 6 ክለቦች ወደ ከፍተኛ ሊግ ሲያድጉ 4 ክለቦች ከከፍተኛ ሊግ ወደ ብሄራዊ ሊግ ይወርዳሉ፡፡ ከክልል ክለቦች ቻምፒየንሺፕ ደግሞ 8 ክለቦች ወደ ብሄራዊ ሊጉ ያደጋሉ፡፡
ጠቃሚ ነጥቦች በዘንድሮው ብሄራዊ ሊግ ላይ . . .
* ውድድሩ በተመሳሳይ ሳምንት እንዲጠናቀቅ በሚል አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ቡድኖችን የያዙ ምድቦች በመሃል እረፍት አድርገዋል፡፡ በዚህም መሰረት 9 ቡድኖች የያዙት መካከለኛው ዞን ሀ እና ደቡብ ዞን ለ በተከታታይ ሳምንታት ጨዋታ ሲያደርጉ 8 ቡድኖች የያዙት መካከለኛው ዞን ለ እና ምስራቅ ዞን በመሃል አንድ ሳምንት እረፍት አድርገዋል፡፡ ሰሜን ዞን ሀ በመሃል ሁለት ሳምንታት ፣ ሰሜን ዞን ለ እና ደቡብ ዞን ሀ ሶስት ሳምንታት አርፈዋል፡፡
* የደቡብ ዞን ሀ የመጀመርያዎቹ ሁለት ሳምንታት ጨዋታዋች በፀጥታ ችግር ምክንያት ሳይካሄዱ በመቆየታቸው የዞኑ ጨዋታዎች እረፍት እንዲያደርጉ በተያዘላቸው ጊዜ ጨዋታውን አድርገዋል፡፡ የሰሜን ዞን ሀ ደግሞ በመሃል ውይይት ለማድረግ አንድ ሳምንት ተቋርጦ እረፍት ሊያደርግ በተያዘለት ጊዜ ተደርጓል፡፡
* በአጠቃላይ በአንደኛው ዙር 168 ጨዋታዎች ሲደረጉ ከነዚህ መካከል ፎርፌ የተሰጠበት ጨዋታ አንድ ነው፡፡ ደባርቅ ከተማ ከዳባት ከተማ በተደረገው ጨዋታ መሃል በተፈጠረ ችግር ምክንያት ችግሩ የተፈጠረው በዳባት ከተማ አማካኝነት ነው በሚል ለደባርቅ ፎርፌ ተወስኖለታል፡፡
* ከ54 ክለቦች መካከል በውድድሩ መሃል ስሙ ላይ ለውጥ የተደረገበት ክለብ ጎጃም ደብረማርቆስ ነው፡፡ ክለቡ ከደብረማርቆስ ከተማ አስተዳደር ብቻ የሚያገኘውን የገቢ ምንጭ ለማስፋት በማሰብ ስያሜውን ከደብረማርቆስ ከተማ ወደ ጎጃም ደብረማርቆስ መለወጡ ታውቋል፡፡
* በምስራቅ ዞን የሚወዳደረው የድሬዳዋው አሊ ሐብቴ ጋራዥ የሶስት ክለቦችን ውህደት ፈጥሮ በዘንድሮው ውድድር ላይ ቀርቧል፡፡ አምና በብሄራዊ ሊጉ ላይ የተሳተፈው ምስራቅ አየር ምድብ እንዲሁም ከክልል ክለቦች ቻምፒዮንሺፕ ወደ ብሄራዊ ሊግ ያደጉት አሊ ሐብቴ ጋራዥ እና አፍረን ቀሎ ውድድሩን በተናጠል የሚያደርጉበት አቅም ላይ የሚገኙ ባለመሆናቸው ውህደት ፈጥረው በአሊ ሐብቴ ጋራዥ ስም ወደ ውድድር ገብተዋል፡፡
————–*—————-
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሊግ የሳምንቱ ውጤቶች እና የደረጃ ሰንጠረዦን ለማወቅ ይህን ሊንክ ይከተሉ፡- የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሊግ የሳምንቱ ውጤቶች እና የደረጃ ሰንጠረዥ
ማስታወሻ
ከላይ የዘረዘርናቸው የውድድሩ ደንቦች በአመቱ መጀመርያ የሊጎቹ ድልድሎች ሲከናወኑ ይፋ የተደረጉ ናቸው፡፡