ሸገር ደርቢ ዛሬ በቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና መካከል ይደረጋል፡፡ በኢትዮጵያ ታላቁ ደርቢ የሆነው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ በአብዛኛው ደጋፊ በከፍተኛ ትኩረት ከሚከታተለው ጨዋታ መካከል ግንባር ቀደሙ ነው፡፡ በሌሎች የአፍሪካ ሃገራትም ተጠባቂ የሆኑ ደርቢዎች ይገኛሉ፡፡ ሶከር ኢትዮጵያም በምስራቅ አፍሪካ (ሱዳን፣ ኬንያ፣ ዩጋንዳ እና ታንዛኒያ)፣ ሰሜን አፍሪካ (ሞሮኮ፣ ግብፅ እና ቱኒዚያ) እና በጋና የሚደረጉ የተወሰኑትን ታላላቅ ደርቢዎች ለመቃኛት ሞክራለች፡፡
ግብፅ ፡ አል አሃሊ ከ ዛማሌክ
ያለጥርጥር ታላቁ የአፍሪካ ደርቢ በካይሮ ሃያሎቹ በአል አሃሊ እና ዛማሌክ መካከል የሚደረገው ነው፡፡ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ደጋፊ በመላው የአረቡ ዓለም ያላቸው ሁለቱ ክለቦች ለዘመናት በባላንጣነት ቆይተዋል፡፡ ካፍ አል አሃሊን የምዕተ ዓመቱ ምርጥ የአፍሪካ ክለብ ብሎ የሰየመ ሲሆን ይህ ለዛማሌኮች የሚዋጥ አይደለም፡፡ የቻምፒየንስ ሊጉን ዋንጫ አምስት እና ከዚያ በላይ ግዜ ያነሱት ሁለቱ ክለቦች ሊጉም ከፍተኛ ተፎካካሪ መሆናቸው የካይሮ ደርቢን ውጥረት እንዲነግስበት አስችሏል፡፡
-በ1909 እ.ኤ.አ የተመሰረተው አሃሊ በብሄርተኛ አና ፀረ-ቅኝ ግዛት ደጋፊዎች ይደገፍ ነበር፡፡ በ1911 የተመሰረተው ዛማሌክ በሃብታሞች የሚደገፍ ክለብ ነበር፡፡
-የሁለቱን ክለቦች ጨዋታ እንዲዳኙ የሚደረጉት ከአውሮፓ የሚመጡ ዳኞች ናቸው፡፡
-የካይሮ ደርቢን አል አሃሊ ከዛማሌክ በተሻለ ብዙ ግዜ ማሸነፍ ችሏል፡፡
-ደርቢው ከእግርኳስ አልፎ በመረብ ኳስ እና የእጅ ኳስ ውድድሮች ላይ ተፎካካሪ ናቸው፡፡
ሞሮኮ – ዋይዳድ ክለብ አትሌቲክ ከ ራጃ ክለብ አትሌቲክ
የካዛብላንካ ደርቢ በዋይዳድ እና ራጃ መካከል ይደረጋል፡፡ አስገራሚ የስታዲየም (ጨዋታው ብዙ ተመልካች መያዝ በሚችለው በስታደ መሃመድ አምስተኛ ይደረጋል) ድባብ በሚታይበት በዚህ ደርቢ በካዛብላንካ ከተማ የሚገኙ ሱቆች ከጨዋታው መጀመር ጥቂት ሰዓታት ቀደም ብለው ይዘጋሉ፡፡ ዋይዳድ እና ራጃ የሞሮኮ ታላላቅ ክለቦች ናቸው፡፡ ዋይዳድ መካከለኛ ገቢ ባለው የህብረተሰብ ክፍል ሲደገፍ አብዛኛውን የደርቢ ግጥሚያ ማሸነፍ የቻለው ራጃ በሰራተኛው መድብ ከፍተኛ ድጋፍን ያገኛል፡፡
– የነውጠኛ ደጋፊዎች ረብሻ በማያጣው የሁለቱ ክለቦች ግጥሚያ በ2007 አንድ የዋይድ ደጋፊ ሊሞት ችሏል፡፡
ቱኒዚያ – ኤስፔራንስ ደ ቱኒዝ ከ ኤቷል ደ ሳህል
ኤቷል እና ኤስፔራንስ የቱኒዚያ ታላላቅ ክለቦች መሆናቸው በሁለቱ መካከል የሚደረገው ጨዋታ የሃገሪቱ ታላቅ ደርቢ ነው፡፡ ኤቷል የሶስ ከተማ ተወካይ ሲሆን ኤስፔራንስ የዋና ከተማዋ ቱኒዝ ክለብ ነው፡፡ ሁለቱም ክለቦች በየውድድር ዘመኑ ለሻምፒዮንነት መጫወታቸው እንዲሁም በአፍሪካ መድረክ ያላቸው ገናና ስም ደርቢው ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ሆኖ እንዲካሄድ አስችሏል፡፡
ክለብ አፍሪካ ከ ኤስፔራንስ ደ ቱኒዝ
ቱኒዚያ የአራት ታላላቅ ክለሎች ባለቤት ናት፡፡ የቱኒዞቹ ኤስፔራንስ እና ክለብ አፍሪካን፣ ሲኤስ ሴፋክሲየን እንዲሁም ኤቷል ስፖርቲቭ ደ ሳህል የቱኒዚያ ታላላቅ ክለቦቸ ናቸው፡፡ ክለብ አፍሪካ እና ኤስፔራንስ የቱኒዚያን ሊግ 1 በተደጋጋሚ ከማሸነፍ አልፎ በቻምፒየንስ ሊግ ይሁን ኮንፌድሬሽን ካፕ የተሻለ ውጤት አላቸው፡፡ ደርቢው 60 ሺህ ተመልካች የመያዝ በሚችለው በስታደ ኦሎምፒክ ራደስ ይካሄዳል፡፡
የቱኒዝን የኢኮኖሚ ዝቅተኛ ክፍል የሚወክለው ኤስፔራንስ ከሃብታሙ መደብ ከፍተኛ ድጋፍ ከሚያገኘው ክለብ አፍሪካን ተመሳሳይ የሆነ የደገፊ ቁጥር አለው፡፡
ጋና – አሻንቴ ኮቶኮ ከ አክራ ሃርትስ ኦፍ ኦክ
የኩማሲው አሻንቴ ኮቶኮ ከጋና ርዕሰ መዲና ሃርትስ ኦፍ ኦክ የሚደርጉት ግጥሚያ የጋና ታላቁ ደርቢ ነው፡፡ የጋናን ፕሪምየር ሊግ 24 በማሸነፍ ባለሪከርድ የሆነው ኮቶኮ በምስረታ ደረጃ ከሃርትስ ኦፍ ኦክ ዘግይቶ ቢሆንም ከ1960ዎቹ ጀምሮ ሁለቱ ክለቦች የሃገሪቷ ቀንደኛ ተፎካካሪ ናቸው፡፡
ስለደርቢ አስተያየቱን ለሶከር ኢትዮጵያ የሰጠው የጋና ሶር ኔት ድረገፅ ሪፖርተሩ ኑሁ አደምስ ክለቦች ከፍተኛ ቁጥር ያለው ደጋፊ ስላላቸው ደርቢው ሁሌም ተጠባቂ ነው፡፡ “ሁለቱም የጋና ስኬታማ ክለቦች ናቸው፡፡ ቻምፒየንስ ሊጉን ማሸነፍ የቻሉ ሲሆን በጋና ከፍተኛ ደጋፊ እና ተከታይ ስላላቸው ሁሌም ደርቢው ይጠበቃል፡፡”
– በ2001 በጋና ደርቢ በተፈጠረ የስታዲየም ግርግር 127 ደጋፊዎች ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡
ሱዳን – አል ሂላል ከ ኤል-ሜሪክ
የሱዳን ታላላቅ ክለቦች ናቸው፡፡ የደርቢ ጨዋታቸው ኦምዱሩማን ደርቢ ይሰኛል፡፡ በሃገሪቱ የሚገኙ ታላላቅ ክቦች ሲሆኑ አል ሂላል ለ25 ግዜ የሱዳን ፕሪምየር ሊግን በማሸነፍ ባለሪከርድ ነው፡፡ የሃይል አጨዋወት እና ዕልህ አስጨራሽ ፉክክር የሚታይበት ይህ ደርቢ ውጥረት የነገሰበት እና በአስደማሚ የደጋፊዎች ድባብ ታግዞ የሚደረግ ነው፡፡
በ1992 ሂላል አል ሳሂል የሊጉን ዋንጫ ካነሳ በኃላ የሊጉ ዋንጫ ከሂላል ውይም ሜሪክ ወጥቶ አለማወቁ ምን ያህል የሱዳንን እግርኳስ እንደተቋጣጠሩት ያሳያል፡፡
ሱዳናዊው የእግርኳስ ጋዜጠኛ አብዱል ሙሳ ደርቢው ከ50 ዓመታት በፊት መጀመሩን ይናገራል፡፡ “ደርቢው ከ50 ዓመታት በፊት ነው የተጀመረው፡፡ ሁለቱን ክለቦች የሚለየው አንድ መንገድ መሆኑ እንዲሁም በሱዳን እግርኳስ ታሪክ ከፍተኛ ተፎካካሪ መሆናቸው ደርቢው ሁሌም የሚናፈቁ ሆኗል፡፡”
ዩጋንዳ – ኤክስፕረስ ከ ስፖርት ክለብ ቪላ
ዩጋንዳ ሁለት ትልልቅ ደርቢዎች አሏት፡፡ በካምፓላ የሚገኙት ካምፓላ ሲቲ ካውንስል፣ ስፖርት ክለብ ቪላ እና ኤክስፕረስ ውጥረት የነገሰበት ጨዋታን ያሳያሉ፡፡ የቺምፒ ሪፖርትስ የስፖርት ዘጋቢ የሆነው ፍሬድ ሙዋምባ የካምፓላ ሲቲ ከ ቪላ የሚያደርጉት ጨዋታ ክላሲኮ ሲል ያሞካሸዋል፡፡ “የካምፓላ ሲቲ ከ ቪላ የሚያደርጉት ደርቢ ክላሲኮ ነው፡፡ ኤክስፕረስ ከቪላ ሁሌም ብጥብጥ የማያጣው እና ከፍተኛ ውጥረት ስላለው ትልቁ የዩጋንዳ ደርቢ ነው፡፡”
– በካምፓላ ደርቢ ኤክስፕረስ ከቪላ ካለፉት አምስት ግንኙነቶች አንዱ ብቻ ተጠናቅቋል፡፡ አራቱ ጨዋተዎች በደጋፊዎች ነውጥ እና በተጫዋቾች ያልተገባ ባህርይ ተቋርጠዋል፡፡
ታንዛኒያ – ያንግ አፍሪካንስ ከ ሲምባ
ሶከር ኢትዮጵያ ያነጋገረቻቸው አብዛኞቹ ጋዜጠኞች የምስራቅ አፍሪካ ታላቁ ደርቢ ዳር ደርቢ ነው የሚል ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡ በአይስክሬም አምራች ድርጅት ስር የሚተዳደረው አዛም የኃይል ሚዛኑን ከሲምባ ከመውሰዱ ውጪ ያንግ አፍሪካንስ ከሲምባ አሁንም የሃገሪቱ ታላቅ ደርቢ ነው፡፡ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ደጋፊ የሚከታተለው ደርቢው በናሽናል ስታዲየም ይደረጋል፡፡
በአፍሪካ መድረክ የሁለቱ ክለቦች ደጋፊዎች ተቃራኒ ቡድንን በመደገፍ ይታወቃሉ፡፡ በ2014 የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታ ያንጋ የግብፁን አል አሃሊን ሲስተናግድ 20ሺህ የሲምባ ደጋፊዎች ለአሃሊ ድጋፋቸው ለመስጠት ወደ ስታዲየም ገብተዋል፡፡
ኬንያ – ኤኤፍሲ ሊዮፖርድስ ከ ጎር ማሂያ
የናይሮቢ ደርቢ ኤኤፍሲ ሊዮፖርድስ ብዙ ግዜ በማሸነፍ የተሻለ ነው፡፡ ጎር ማሂያ 23 ጨዋታዎችን ሲያሸንፍ ሊዮፖርድስ በ28 ጨዋታዎች አሸነፊ ነው፡፡
ማሺሚጂ ደርቢ ወይም ኢንጎ-ዳላ ደርቢ በመባል በሚታወቅው ይህ ደርቢ በኬንያ ታላቁ እና ብዙ ውጥረት የሚታይበት ነው፡፡ ጎር ማሂያ 15 ግዜ የኬንያ ሻምፒዮን በመሆን ባላሪከርድ ሲሆን ከ1968 ጀምሮ የሊዮፖርድስ ባላንጣ ነው፡፡ ከ2000 መጨረሻ ጀምሮ የደጋፊዎች ረብሻ የማያጣው ይህ ደርቢ በተደጋጋሚ በሚነሱ ግጥቶች ክለቦቹን ለቅጣት ዳርገዋል፡፡
ከላይ ከተጠቀሱት ባሻገር በደቡብ አፍሪካ የሶዌቶ ደርቢ (ካይዘር ቺፍስ ከ ኦርላንዶ ፓያሬትስ) ፣ በአይቮሪኮስት የአቢጃን ደርቢ (አሴክ ሚሞሳ ከ አሴክ አቢጃን) ፣ በአልጄሪያ የአልጀርስ ደርቢ (ጄኤስ ካቢሊ ከ ዩኤስኤም አልጀር ፣ ዩኤስኤም አልጀር ከኤምሲ አልጀር) በሞሮኮ የራባት ደርቢ (ፉስ ራባት ከ ፉር ራባት) ፣ በሩዋንዳ ኪጋሊ ደርቢ (ኤፒአር ከ ራዮን) በኮንጎ ዲ.ሪ. የኮንጎ ደርቢ (ቲፒ ማዜምቤ ከ ቪታ ) ፣ በካሜሩን የያውንዴ ደርቢ (ካኖን ያውንዴ ከቶኔር ያውንዴ) ይጠቀሳሉ፡፡