ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | መቐለ 70 እንደርታ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | መቐለ 70 እንደርታ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

ነገ በታሪካቸው ለ6ተኛ ጊዜ የሚገናኙት ቡድኖች የሚያፋልመው ጨዋታ ምዓም አናብስት ከሽንፈት ለማገገም ፈረሰኞቹ ደግሞ በያዙት የአሸናፊነት መንገድ ለመዝለቅ በእጅጉ ይፈልጉታል።

ከሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች መልስ ሀድያ ሆሳዕናን ሁለት ለባዶ በማሸነፍ መጠነኛ እፎይታ አግኝተው የነበሩት ምዓም አናብስት በመጨረሻው ሳምንት በባህርዳር ከተማ ከገጠማቸው ሽንፈት አገግመው ካንዣበበባቸው የወራጅ ቀጠና ስጋት ለመላቀቅ ፈረሰኞቹን ይገጥማሉ።

መቐለ 70 እንደርታ በቅርብ ሳምንታት ጉልህ የሆኑ ግለ ሰባዊ እና መዋቅራዊ የመከላከል ስህተቶች ተስተውሎበታል፤ በመጨረሻው ጨዋታ ግን ይባስ ብሎ በመጀመርያዎቹ አስራ ስድስት ደቂቃዎች ሦስት ግቦች በማስተናገድ በጨዋታው አራት ለአንድ በሆነ ውጤት ሽንፈት ለማስተናገድ ተገዷል።

ይህንን ተከትሎ በጨዋታው የታዩ ጉልህ የመከላከል ድክመቶች መቅረፍ የቡድኑ ቀዳሚ የቤት ስራ መሆን ይገባዋል፤ በተለይም በተደጋጋሚ ጊዜ የተስተዋሉት ሰፊ ክፍት ቦታዎች የመከላከል እና የመልሶ ማጥቃቶች የማቆም ችግር አንገብጋቢ መፍትሔ የሚሹ ድክመቶች ናቸው። ቡድኑ በጨዋታው በሰፊ የግብ ልዩነት ቢሸነፍም በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ ውስን ተስፋ ሰጪ ነገሮች አሳይቷል፤ የግብ ዕድሎች በመፍጠር እና ሙከራዎች ለማድረግ የነበረው ጥረትም ወደ ነገው መርሐ-ግብር መሻገር የሚገባው አወንታዊ ጎን ነው። 

በሊጉ ለመቆየት በሰንጠረዡ የታችኛው ክፍል በሚደረገው ፉክክር ልቆ መገኘት በሚጠይቀው ወሳኝ ወቅት የሚገኙት ምዓም አናብስት ከመጨረሻው ሳምንቱ አስከፊ ሽንፈት መልስ በአዕምሮ እና በአካላዊ ዝግጁነት ላይ አተኩረው ወደ ሜዳ መግባት ይጠበቅባቸዋል።

በሰለሣ አራት ነጥቦች 10ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ቅዱስ ጊዮርጊስ በመጨረሻው ሳምንት ከስምንት መርሐ-ግብሮች በኋላ ባስመዛገበው ድል መጠነኛ እፎይታ አግኝቶ በሰንጠረዡ አጋማሽ ረግቷል።

ፈረሰኞቹ በስምንት የጨዋታ ሳምንታት ማግኘት ከሚገባቸው ሀያ አራት ነጥቦች ሦስቱን ብቻ ማሳካታቸው ተከትሎ ከመሪዎቹ ጎራ ተነጥለው ወደ ሰንጠረዡ አካፋይ እንዲቀመጡ ሆኗል። ቡድኑ ገጥሞት ከነበረው አሉታዊ ውጤት በመውጣት በመጨረሻው ጨዋታ ወልዋሎን ማሸነፍ ቢችልም ያለበት ደረጃ ግን ከስጋት ቀጠናው ሩቅ አይደለም። 
በወራጅ ቀጠናው አፋፍ ከሚገኘው የነገው ተጋጣሚው መቐለ ያለው የነጥብ ልዩነት ስድስት ብቻ መሆኑም ይህንን ለማለት በቂ ነው። ይህንን ተከትሎም በነገው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ማግኘት አስፈላጊው ነው፤ ይህ እንዲሳካ ግን በስምንት መርሐ-ግብሮች ሁለት ግቦች ብቻ ካስቆጠረ በኋላ በመጨረሻው ጨዋታ ሦስት ግቦች ማስቆጠር የቻለው የማጥቃት ጥምረቱ አወንታዊ ለውጥ ማስቀጠል ግድ ይላቸዋል።

በነገው ጨዋታም የውድድር ዓመቱ ጉዞውን ለማቃናት አስፈላጊ ድል ፍለጋ ወደ ሜዳ የሚገባ ቡድን እንደመግጠማቸው በብዙ ረገድ ተሻሽለው መቅረብ የሚኖርባቸው ሲሆን ባለፉት መርሐ-ግብሮች በቡድኑ ላይ የታየው በሁለቱም አጋማሾች በተመሳሳይ ፍጥነት እና ፍላጎት የመጫወት የወጥነት ችግርም ሌላው ቡድኑ ሊቀርፈው የሚገባው ደካማ ጎን ነው። 

መቐለ 70 እንደርታዎች ያብስራ ተስፋዬ በእግድ ምክንያት፤ ሄኖክ አንጃው እና ቦና ዐሊ በጉዳት፤ ግብ ጠባቂው ምሕረትአብ ገብረህይወት ደግሞ በህመም እንዲሁም ኢማኑኤል ላርያ በቅጣት ምክንያት አያሰልፉም፤ አማካዩ ኬኔዲ ገብረፃዲቅ ግን ገጥሞት ከነበረው ሕመም አገግሞ ለነገ ጨዋታ ዝግጁ ሆኗል። በፈረሰኞቹ በኩል በጉዳት የከረሙት አማካዩ አብዱልሀፊዝ ቶፊቅ እና አጥቂው ተገኑ ተሾመ ከጉዳታቸው አገግመው ወደ ሀዋሳ ከተጓዘው ስብስብ ተቀላቅለዋል። ከዚህ በተጨማሪ ፍሪምፖንግ ክዋሜ እና ፉአድ ዓብደላ በጉዳት ከቡድኑ ጋር የማይገኙ ሲሆን ሻይዱ ሙስጠፋም ከጉዳቱ አገግሞ ከቡድኑ ጋር ተቀላቅሎ ልምምድ ቢጀምርም ለነገው ጨዋታ የማይደርስ እንደሆነ ታውቋል። ከዚህ ውጭ ቡድኑ 20 ተጫዋቾችን በመያዝ ሀዋሳ ከተማ መግባቱን አረጋግጠናል።

ሁለቱ ቡድኖች 5 ጊዜ ተገናኝተው አንድ አንድ ጊዜ ሲሸናነፉ በሦስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል፤ በጨዋታዎቹም 3 ግቦች በእኩሌታ ማስቆጠር ችለዋል። (በ2012 የተሰረዘውን ጨዋታ አያካትትም)