ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ወላይታ ድቻ ከ አርባምንጭ ከተማ

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ወላይታ ድቻ ከ አርባምንጭ ከተማ

ባለፉት አራት ጨዋታዎች ተመሳሳይ ውጤት ያስመዘገቡ በሦስት ነጥቦች የሚበላለጡ ቡድኖች የሚያገናኘው ጨዋታ ተጠባቂ ነው።

በሰላሣ ስምንት ነጥቦች 7ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ወላይታ ድቻዎች ከአራት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል መንገድ ለመመለስ አዞዎቹን ይገጥማሉ።

የጦና ንቦቹ ሁለተኛውን ዙር መሪው መድን በማሸነፍ ጀምረው ሦስት ተከታታይ ድሎች በማስመዝገብ አስደናቂ ግስጋሴ ማድረግ ቢችሉም ቀጥለው በተካሄዱ አራት ጨዋታዎች ግን ከድል ጋር ተራርቀዋል፤ ውጤቱን ተከትሎም ከመሪዎቹ ጎራ ተነጥለው ወደ ሰንጠረዡ አካፋይ ተንሸራተዋል። ለዚህ እንደ ምክንያት የሚጠቀሰው ደግሞ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው የግብ ማስቆጠር ድክመት ሲሆን ቡድኑ ከሽንፈት በራቀባቸው ስድስት ውጤታማ መርሐ-ግብሮች ላይ በጨዋታ በአማካይ ከአንድ ግብ በላይ ማስቆጠር አለመቻሉም ችግሩ ዘለግ ላሉ ጊዜያት መቆየቱ ማሳያ ነው። ሁለት ሽንፈቶችና ሁለት የአቻ ውጤቶች ባስመዘገቡባቸው እና ማግኘት ከሚገባቸው አስራ ሁለት ነጥቦች ሁለቱን ብቻ ካሳኩባቸው ድል አልባ ጨዋታዎች ለማገገምም የተጠቀሰው የግብ ማስቆጠር ድክመት ማረም ይገባቸዋል።

ሰላሣ አምስት ነጥቦች በመሰብሰብ ከነገው ተጋጣሚያቸው በሦስት ነጥቦች አንሰው 11ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት አርባምንጭ ከተማዎች ወደ ነበሩበት የሰንጠረዡ ወገብ ለመጠጋት ድል ማድረግ አስፈላጊያቸው ነው።

አዞዋቹ እንደ ተጋጣሚያቸው ሁሉ ባለፉት አራት ጨዋታዎች ሁለት ሁለት የአቻ እና የሽንፈት ውጤቶች በማስመዝገብ ለአራት የጨዋታ ሳምንታት ከድል ጋር ተራርቀዋል። ለቡድኑ ውጤት መቀዛቀዝ እንደ ምክንያት የሚጠቀሰው ደግሞ ከዚህ ቀደም የቡድኑ ዋነኛ ጠንካራ ጎን የነበረው የማጥቃት ጥምረቱ መዳከም ነው። አዞዎቹ በሁለተኛው ዙር የመጀመርያ አምስት ጨዋታዎች ሰባት ግቦች ካስቆጠሩ ወዲህ በሊጉ የመጨረሻ ሦስት መርሐ-ግብሮች ኳስና መረብ ማገናኘት አለመቻላቸው እንዲሁም በጨዋታዎቹ እንደ ወትሮ በርከት ያሉ የግብ ዕድሎች ለመፍጠር መቸገራቸው ስለ ፊት መስመሩ አሁናዊ ብቃት ምስክሮች ናቸው።

ይህንን ተከትሎ የቀድሞ ውጤታማ ቀጥተኛ እና የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ጥንካሬ መመለስ የአሰልጣኝ በረከት ደሙ ቀዳሚ የቤት ስራ መሆን ይገባዋል። ከዚህ በተጨማሪ በውድድር ዓመቱ ሀያ ስድስት ግቦች አስቆጥሮ ሀያ ስድስት ግቦች ያስተናገደው ቡድኑ በመከላከሉ ረገድ ያሉበት ክፍተቶች ማረምም ሌላው የሚጠብቀው የቤት ስራ ነው።

በወላይታ ድቻ በኩል የግራ መስመር ተከላካዩ ፍፁም ግርም በቅጣት ምክንያት አይሰለፍም። ባለፉት ጨዋታዎች ላይ ያልተሳተፉት አዛርያስ አቤል እና ኬኔዲ ከበደ ግን ወደ ልምምድ መመለሳቸውን ተከትሎ በጨዋታ ዕለት ስብስቡ ይካተታሉ ተብሎ ሲጠበቅ  ሌሎቹ የቡድኑ አባላትም ለነገው ጨዋታ ዝግጁ መሆናቸው ታውቋል። በአርባምንጭ ከተማ በኩል በፍቅር ግዛው ፣ፀጋዬ አበራ እና አሸናፊ ፊዳ በጉዳት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጪ መሆናቸው ሲረጋገጥ ሌሎች የቡድን አባላቶች ግን ለነገው ጨዋታ ልምምድ እየሰሩ መሰንበታቸውን አረጋግጠናል።

ከዚህ ቀደም ሁለቱ ቡድኖች 15 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን 9 ጨዋታዎች ነጥብ በመጋራት ሲፈፅሙ ወላይታ ድቻዎች 4 እንዲሁም አርባምንጭ ከተማዎች ደግሞ 2 ጊዜ ማሸነፍ ችለዋል።