ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ኢትዮጵያ መድን ከ ባህርዳር ከተማ

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ኢትዮጵያ መድን ከ ባህርዳር ከተማ

ኢትዮጵያ መድን እና ባህርዳር ከተማ የሚያፋልመው በዋንጫ ፉክክሩ ትልቅ ትርጉም ያለው ጨዋታ የሊጉን ተከታታዮች ሁሉ ትኩረት የሳበ ሆኗል።

በሰባት ተከታታይ ጨዋታዎች ሁለት ነጥቦች ብቻ ጥለው ተከታታይ ድሎች በማስመዝገብ መሪነታቸውን አጥብቀው የያዙት መድኖች የዋንጫው አንድ እጀታ ለመጨበጥ የሚያስችላቸውን ዕድል ለማመቻቸት በ3ኛ ደረጃ ከተቀመጡት የጣና ሞገዶቹ ይፋለማሉ።

በአመዛኙ ከመከላከል ወደ ማጥቃት በሚደረግ ፈጣን ሽግግሮች የተጋጣሚን የግብ ክልል መጎብኘት የሚያዘወትረው ቡድኑ ነገም እንደ ወትሮ በተመሳሳይ አቀራረብና የጨዋታ መንፈስ የሚቀርብ ከሆነ ለተጋጣሚው ቡድን ፈተና ነው። ቡድኑ ላቅ ያለው የአፈፃፀም ብቃቱ ይዞ ከመዝለቁም በተጨማሪ በፊት መስመር ያለውን የግብ ማስቆጠርያ መንገድ አማራጩን አስፍቷል፤ ባለፉት ሰባት  ጨዋታዎች አስራ ሦስት ግቦች ማዝነቡም የፊት መስመሩ ያለበት አሁናዊ ብቃት ማሳያ ነው። ቡድኑ ወሳኝ በሚባለው የውድድር ወቅት የፊት መስመር ጥምረት ጥንካሬውን ማስቀጠሉ እንደ አወንታ የሚነሳለት ጉዳይ ቢሆንም ተጋጣሚው ጥቂት ግቦች በማስተናገድ በ2ኛ ደረጃ የተቀመጠና ካለፉት ስምንት ጨዋታዎች ውስጥ በአምስቱ መረቡን ባለማስደፈር ሁለት ግቦች ብቻ ያስተናገደ መሆኑ ሲታይ ግን የሚጠብቀው ፈተና ቀላል እንደማይሆን መገመት ይቻላል።

ከዚ በተጨማሪ በፈጣኖቹ አጥቂዎች የሚመራው የጣና ሞገዶቹ የፊት መስመር በነገው ጨዋታ ለቡድኑ ከባድ ፈተና እንደሚሆን ይታሰባል። ከምንም በላይ በሽግግሮችና በሁለቱም መስመሮች ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ የማያቅተውን ተጋጣሚ ለመግታትም ልዩ ዝግጅት ማድረግ ሳይኖርባቸውም አይቀርም።

በአርባ ሦስት ነጥቦች 3ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት የጣና ሞገዶቹ  መቐለ 70 እንደርታና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ላይ ስድስት ግቦች አስቆጥረው ከረቱ በኋላ ለነገው ጨዋታ ይደርሳሉ።

ባህርዳር ከተማ ደካማ የተጋጣሚ የመከላከል አደረጃጀት ወይንም ለፈጣን ጥቃቶች የተመቸ ተጋላጭ የሆነ ቡድኑ ካገኘ ተደጋጋሚ የግብ ዕድሎችን መፍጠር እንዲሁም ለውጤት ማብቃት እንደሚችል ባለፉት ጨዋታዎች ደጋግሞ አሳይቶናል። ተጋጣሚያቸው መድን በሊጉ አስር ግቦች ብቻ ያስተናገደ እና ጠንካራ የመከላከል ውቅር የገነባ ቡድን ቢሆንም ባለፉት አራት መርሐ-ግብሮች በጨዋታ በአማካይ ሁለት ግቦች ያስቆጠረ በውጤታማ አሁናዊ ብቃት የሚገኘው የጣና ሞገዶቹ የማጥቃት አጨዋወትም ቀላል ፈተና እንደማይሆን የታወቀ ነው። በባህርዳር ከተማዎች በኩል በጨዋታው ትልቁ የቤት ስራ ሊሆን የሚገባው የኋላ ክፍላቸው ጉዳይ ነው፤ እርግጥ የቡድኑ የመከላከል አደረጃጀት ጠጣር እና በቀላሉ ለጥቃት የማይጋለጥ ቢሆንም ከተጋጣሚው ወቅታዊ ብቃት አንፃር ለሚገጥመው ፍልምያ ከመቼውም ጊዜ በላይ ጠንካራ መሆን ወሳኝነት አለው።

በቅርብ ሳምንታት በርካታ ግቦች እያስቆጠሩ እዚህ የደረሱት በአስራ አንድ ነጥቦች የሚበላለጡ ሁለት ቡድኖች የሚያገናኘው ጨዋታ ማራኪ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል። መድን ከተከታዮቹ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ አስራ ሁለት ከፍ ለማድረግ ባህርዳር ከተማ ደግሞ በዋንጫ ፉክክሩ ነፍስ ሊዘሩ የሚችሉ ሦስት ነጥቦች ለማግኘት ከሚደረገው ፉክክር በተጨማሪ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ያለው ውጤታማው የፊትና የኋላ ጥምረቶች   የሚያደርጉት ፍልምያም ጨዋታው አጓጊ ያደርገዋል።

በባህር ዳር ከተማ በኩል ሁሉም የቡድን አባላት ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው። በመድን በኩል ያለው የቡድን ዜና ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ግን አልተሳካም።

ቡድኖቹ በሊጉ 5 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ኢትዮጵያ መድን 2 ጊዜ ባህርዳር ከተማ ደግሞ 1 ጊዜ ድል ስያደርጉ 2 ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርተዋል። 15 ግቦች በተቆጠሩበት የሁለቱም ግንኙነት መድን 8 ባህርዳር ደግሞ 7 ግቦች አስቆጥረዋል።