ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ኢትዮጵያ ቡና ከ ወላይታ ድቻ

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ኢትዮጵያ ቡና ከ ወላይታ ድቻ

በአራት ነጥብ ልዩነት ተከታትለው የተቀመጡትን ቡናማዎቹ እና የጦና ንቦቹ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።

አርባ አምስት ነጥቦች በመሰብሰብ 3ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኢትዮጵያ ቡናዎች ኢትዮጵያ መድን በትናንትናው ዕለት ሽንፈት ማስተናገዱን ተከትሎ ከመሪው ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ወደ ዘጠኝ ጠቧል፤ ከነገው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ይዞ መውጣትም መሪው ላይ ጫና ለማሳደር ዕድል ስለሚፈጥርላቸው የመርሐ-ግብሩ ወሳኝነት ትልቅ ነው።

ቡናማዎቹ በሲዳማ ቡና ሽንፈት ካስተናገዱበት ጨዋታ አገግመው በተከታታይ ሁለት መርሐ-ግብሮቹ ሙሉ ነጥብ ማግኘት ቢችሉም በዋንጫ ፉክክሩ እስከመጨረሻው ድረስ ለመዝለቅ ለግብ ማስቆጠር ችግራቸው ዘላቂ መፍትሔ ማበጀት ይኖርባቸዋል። ቡድኑ በ2ኛው ዙር በተካሄዱ ዘጠኝ ጨዋታዎች ውስጥ በሰባቱ መረቡን በማስከበር የመከላከል ጥንካሬው ማስቀጠሉ አሁንም የዋንጫ ተፎካካሪ ሆኖ ሊቀጥል እንደሚችል ፍንጭ የሚሰጥ ቢሆንም የፊት መስመሩ ጥንካሬ ግን ደረት የሚያስነፋ አይደለም። በዘጠኝ ጨዋታዎች ሰባት ግቦች ብቻ ያስቆጠረው ቡድኑ በቅርብ ሳምንታት ከበላዩ ከተቀመጡት የቅርብ ተፎካካሪዎቹ አንፃር ሲታይ ያነሰ የግብ መጠን አስቆጥሯል፤ ይሄ የአፈፃፀም ድክመትም ምናልባትም ከፉክክሩ እንዳይዘልቅ ልያደርገው ስለሚችል ካሁኑ ችግሩን ማረም  ይጠበቅበታል። 

በአርባ አንድ ነጥቦች 4ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ወላይታ ድቻዎች ከነገው ተጋጣሚያቸው ኢትዮጵያ ቡና በአራት ነጥቦች ርቀት ላይ ይገኛሉ። በመሆኑም ከተጋጣሚያቸው ጋር ተጨማሪ ክፍተት እንዳይፈጠር እንዲሁም ደረጃቸውን ላለማጣት ድል እጅግ አስፈላጊያቸው ይሆናል።

በመጨረሻው ጨዋታ አዞዎቹን በማሸነፍ ወደ ድል መንገድ የተመለሱት የጦና ንቦቹ ከድል ጋር በተራራቁባቸው አራት የጨዋታ ሳምንታት ካሳዩት መዘቃቀዝ መልስ ድል ማድረጋቸው ደረጃቸው እንዲያሻሽሉ ረድቷቸዋል። ቡድኑ ማግኘት ከሚገባው አስራ ሁለት ነጥቦች ሁለቱን ብቻ ባሳካባቸው ከ24 ኛው እስከ 28 ኛው ሳምንት በተካሄዱ ጨዋታዎች ያስመዘገባቸው ውጤቶች ከብዙዎች ግምት ውጭ ነበር። ውጤቶቹ
በወራጅ ቀጠናው የሚገኙ ሦስት ክለቦች በገጠመባቸው በአንፃራዊነት ቀላል ፉክክር በነበረባቸው መርሐ-ግብሮች መመዝገባቸው እንዲሁም አንድ ነጥብ ብቻ ከከሰረባቸው እጅግ ውጤታማ ስድስት የጨዋታ ሳምንታት በኋላ የተመዘገቡ መሆናቸው ብዘዎቹን ያስገረመ ነበር። የጦና ንቦቹ ብርቱ ፉክክር ከተደረገበት የአርባምንጩ ጨዋታ ውጤት ይዘው ከመውጣታቸው ባለፈ ያሳዩት እንቅስቃሴ በነገው ዕለት ቀላል ተጋጣሚ እንደማይሆኑ ማሳያ ነው። በተለይም በ14ኛው ሳምንት ጨዋታ ወልዋሎ ላይ ሁለት ግቦች ካስቆጠረ በኋላ በተካሄዱ አስራ ሦስት መርሐ-ግብሮች በጨዋታ ከአንድ ግብ በላይ ሳያስቆጥር የቆየው እና በጨዋታው ሁለት ግቦችን ከመረብ ጋር ያዋሃደው የማጥቃት ክፍሉ የተገኙ ዕድሎች በመጠቀም ረገድ ያሳየው ለውጥ በጥሩነቱ ይነሳላቸዋል። ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ግቡን ያላስደፈረውን ቡና በሚገጥሙበት ጨዋታም ይህንን ጥንካሬ ማስቀጠል ከጨዋታው አንዳች ነጥብ ይዘው እንዲወጡ ያግዛቸዋል።

በሁለቱም ቡድኖች መሀል ካለው የነጥብ እና የደረጃ መቀራረብ በተጨማሪ ከኳስ ውጭ ባላቸው ተመሳሳይ የሆነ አቀራረብም ጨዋታው ሳቢ እና ተጠባቂ ያደርገዋል።

በ21 ጊዜ የክለቦቹ የቀደመ ግንኙነት 10 የአቻ ውጤቶች ከፍተኛውን ድርሻ ይዘዋል። በቀሪዎቹ ፍልሚያዎች የጦና ንቦቹ 6 ቡናማዎቹ ደግሞ 5 ጊዜ አሸንፈዋል። በእነዚህ 21 ጨዋታዎች አጠቃላይ 36 ጎሎች ሲቆጠሩ ቡናማዎቹ 18፤ የጦና ንቦቹም በተመሳሳይ18 ግብ በስማቸው አስመዝግበዋል።