የመቻሉ የግብ ዘብ የብሔራዊ ቡድን ጥሪ ደርሶታል

የመቻሉ የግብ ዘብ የብሔራዊ ቡድን ጥሪ ደርሶታል

ዩጋንዳዊው የግብ ዘብ አሊዮንዚ ናፊያን በብሔራዊ ቡድን ግዳጅ ምክንያት ቀጣዮቹ የመቻል ጨዋታዎች ላይ አይሳተፍም።

በ2016 የኢትዮጵያን እግርኳስ የተዋወቀው የመቻሉ የግብ ዘብ አሊዮንዚ ናፊያን ዓምና እና ዘንድሮ በድምሩ 5028 ደቂቃዎች ላይ በመሳተፍ መቻልን እያገለገለ የሚገኝ ሲሆን ግብ ጠባቂዎችን በማውጣት የምትታወቀው ሀገሩ ዩጋንዳንም በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ እንዲሁም በአህጉራዊ ውድድሮች እየወከለ እንደሚገኝ ይታወቃል።

የ29 ዓመቱ ግብ ጠባቂ ሀገሩ ዩጋንዳ ጁን 6 እና 9 ሞሮኮ ላይ ለምታደርጋቸው የካሜሩን እና ጋምቢያ የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎች ጥሪ የደረሰው ሲሆን በትናትናው ዕለትም የመጀመሪያው የዝግጅት ምዕራፍ ወደሚደረግበት ዩጋንዳ ማቅናቱን አውቀናል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዓለም አቀፍ የሀገራት ጨዋታዎች ወቅትን ተጠቅሞ የሚያደርጋቸው የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎች አለመኖራቸውን ተከትሎ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የማይቋረጥ በመሆኑ ተጫዋቹ እስከ 34ኛ ሳምንት ድረስ የሚደረጉ የክለቡ ጨዋታዎች ሊያመልጡት እንደሚችል ይጠበቃል።