በሊጉ ለመሰንበት የሞት ሽረት ትግል ማድረግ የሚጠበቅበት አዳማ ከተማ እና ሀዲያ ሆሳዕና የሚያደርጉት ጨዋታ ረፋድ ላይ ይካሄዳል።
በሀያ ዘጠኝ ነጥቦች 16ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት አዳማ ከተማዎች በሊጉ ለመቆየት በሚያደርጉት ጉዞ ወሳኝ ከሆኑ መርሐግብሮች ውስጥ አንዱ የሆነውን ጨዋታ ነገ ያደርጋሉ።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ሁለት ለባዶ በማሸነፍ የከተማቸውን ቆይታ የጀመሩት አዳማ ከተማዎች ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ባስመዘገቧቸው ነጥቦች በሊጉ የመቆየት ዕድላቸውን አለምልመዋል። ባለፉት አምስት ጨዋታዎች በአንድ አጋጣሚ ብቻ ሽንፈት በማስተናገድ ሁለት የአቻ እና ሁለት ድሎች ያስመዘገቡት አዳማዎች በቅርብ ሳምንታት ከሽንፈት መራቃቸው ከከባዱ ጨዋታ በፊት በሥነ ልቦናው ጠንክረው እንዲቀርቡ የሚያደርጋቸው ጉዳይ ነው።
ቡድኑ ሁለት ነጥብ ብቻ ካስመዘገበባቸው ከ21ኛው እስከ 26ኛው ሳምንት ድረስ በተካሄዱ ስድስት መርሐ-ግብሮች በኋላ ሁለት ወሳኝ ድሎች ከማግኝቱም በላይ በማጥቃቱ እና በመከላከሉ ረገድ የነበሩበትን ድክመቶችንም አርሟል። በተለይም በስድስት መርሐ-ግብሮች አስራ አንድ ግቦችን ካስተናገደ በኋላ በመጨረሻዎቹ አምስት ጨዋታዎች ውስጥ በሦስቱ መረቡን አስከብሮ ሦስት ግቦችን ብቻ ያስተናገደው የመከላከል አደረጃጀቱ የሚታይ ለውጥ አምጥቷል። በ15ኛ ደረጃ ላይ ካለው መቐለ በአራት ነጥብ፤ በሊጉ ለመቆየት ከሚያስችለው 14ኛ ደረጃነት ደግሞ በአምስት ነጥቦች ርቀት ላይ የሚገኘው ቡድኑ የውድድር ዓመቱ ዋነኛው ዕቅዱ ለማሳካት የመከላከል ጥንካሬውን ማስቀጠል እንዲሁም የማጥቃት አጨዋወትን ጥራቱ ይበልጥ ማሳደግ ይኖርበታል።
በአርባ ሦስት ነጥቦች 6ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሀድያ ሆሳዕናዎች ከሁለት ተከታታይ የአቻ ውጤቶች በኋላ ወደ ድል መንገድ ለመመለስ በሊጉ ለመቆየት ወሳኝ ድል በማስመዝገብ ግዴታ ውስጥ ሆኖ የሚቀርበውን አዳማ ከተማ ይገጥማሉ።
ለዋንጫ ከሚደረገው ፉክክር ሆነ ላለመውረድ እየተደረገ ከሚገኘው ፍልሚያ ውስጥ የማይገኙት ነብሮቹ ከቀሩት ጥቂት መርሐ-ግብሮች አንፃር ዋነኛው ዕቅዳቸው በሰንጠረዡ ወገብ ላይ ሆኖ ሊጉን ማጠናቀቅ ይመስላል። ከውድድር ዓመቱ አጋማሽ በኋላ የመጀመርያውን ዙር ውጤታማ ጉዟቸውን ማስቀጠል ያልቻሉት ነብሮቹ የሁለተኛው ዙር አካሄዳቸው በውጣ ውረድ የተሞላ ነበር።
በሁለተኛው ዙር በተደረጉ አስራ ሁለት መርሐ-ግብሮች ውስጥ ሁለት ድሎችን ብቻ ያስመዘገበው ቡድኑ በተለይም አንዴ ሞቅ አንዴ ቀዝቀዝ እያለ በወጥነት መዝለቅ ያልቻለውን የማጥቃት አጨዋወቱን ማሻሻል ይኖርበታል። በነገው ዕለትም ባለፉት አራት ጨዋታዎች ሁለት ግቦችን ብቻ ያስተናገደና በሂደት ወደ ጥሩ ብቃት የመጣ የመከላከል አደረጃጀት ያለው እንዲሁም በሊጉ ለመቆየት የሞት ሽረት ትግል ማድረግ የሚጠበቅበትን ቡድን እንደመግጠማቸው የሚጠብቃቸው ፈተና ከባድ መሆኑ አይቀሬ ነው።
በአዳማ ከተማ በኩል ስንታየሁ መንግሥቱ በአምስት ቢጫ ካርዶች ምክንያት በተላለፈበት የአንድ ጨዋታ ቅጣት በነገው ጨዋታ አይሰለፍም። ከውድድር ዓመቱ ውጪ እንደሆነ ከተጠቆመው አሜ መሐመድ በተጨማሪ መጠነኛ ጉዳት ያጋጠመው ግብ ጠባቂው ዳግም ተፈራም ለጨዋታው የመድረሱ ጉዳይ ነገ የሚረጋገጥ ይሆናል። በሀድያ ሆሳዕና በኩል አስጨናቂ ፀጋዬ ፣ ሄኖክ አርፊጮ እና ተመስገን ብርሀኑ ሲመለሱ ከድር ኩሊባሊ፣ ብሩክ ማርቆስ እና ማሞ አየለ ግን በጉዳት ለነገው ጨዋታ የማይደርሱ ይሆናል። የተቀረው የቡድኑ አባላት ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ናቸው።
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም 11 ጊዜ ተገናኝተው ሀዲያ ሆሳዕና 5 ጊዜ፤ አዳማ ከተማ ደግሞ 3 ጊዜ ሲያሸነፉ 3 ጨዋታዎች አቻ ተጠናቀዋል። አዳማ 11 ሀዲያ ደግሞ 14 ግቦችን አስቆጥረዋል።