ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ወልዋሎ ዓ.ዩ ከ ኢትዮጵያ ቡና

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ወልዋሎ ዓ.ዩ ከ ኢትዮጵያ ቡና

በዋንጫ ፉክክሩ ለመዝለቅ  ከመሪው ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ማጥበብ የሚጠበቅባቸው ቡናማዎቹ መውረዳቸውን ካረጋገጡት ቢጫዎቹ የሚያደርጉት ጨዋታ ቀትር ላይ ይካሄዳል።

በአስራ አምስት ነጥቦች በሊጉ ግርጌ የተቀመጡትና ከሊጉ መውረዳቸውን ያረጋገጡት ወልዋሎዎች የውድድር ዓመቱ አጨራረሳቸውን ለማሳመር እንዲሁም ለክብር በዋንጫ ፉክክሩ አስፈላጊ ድል ለማስመዝገብ ወደ ሜዳ የሚገባውን ኢትዮጵያ ቡና ይገጥማሉ። ውጤት የማስጠበቅ ስር የሰደደ ችግር ያለበት ወልዋሎ በቅርብ ሳምንታት በብዙ ረገድ የተሻሻለ ብቃት ማሳየት ቢችልም በመከላከሉ ረገድ ባሉበት ድክመቶች መነሻነት ውጤት ማስጠበቅ አቅቶት የሽንፈት እንዲሁም የአቻ ውጤቶች ማስመዝገቡን ተከትሎ ቀድሞ ከሊጉ መውረዱን አረጋግጧል። ቡድኑ ከመጨረሻዎቹ አምስት መርሐ-ግብሮች ውስጥ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ባዶ ለባዶ ከተለያየበት ውጭ በተቀሩት ጨዋታዎች እየመራ ነጥብ መጣሉም ለስር የሰደደ ችግሩ ማሳያ ነው።

የነገው ውጤት ይበልጥ የሚያስፈልጉት ኢትዮጵያ ቡና ከመሪው ጋር የተፈጠረውን የዘጠኝ ነጥብ ልዩነት አጥብቦ በፉክክሩ ለመቆየት ሙሉ ነጥብ  በጣሙን ያስፈልገዋል።

እጅግ ማራኪ ፉክክር በታየበት ጨዋታ መሪው መድንን አሸንፈው ወደ ነገው ጨዋታ የሚቀርቡት ቡናማዎቹ በውድድር ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ አምስት ተከታታይ ድሎችን አስመዝግበው ራሳቸውን በዋንጫ ፉክክሩ ያከረሙ ሲሆን በነገው ዕለትም ሲዳማ ቡናን ካሸነፈው መሪው መድን ያላቸውን የዘጠኝ ነጥብ ልዩነት አጥብበው በፉክክሩ ለመዝለቅ መውረዱን ካረጋገጠው ወልዋሎ ጋር ይጫወታሉ።

በምርጥ ወቅታዊ ብቃት ላይ የሚገኘው ቡና በሁለቱም የፍፁም ቅጣት ምት ክልሎች የነበሩበትን ክፍተት በመጠኑ እያሻሻለ ተከታታይ ድሎችን በማስመዝገብ መሪውን እግር በእግር መከተሉን ቀጥሎበታል። ባለፉት አምስት ጨዋታዎች በተገኙት 15 ነጥቦች ምንም ግብ አለማስተናገዱን ደግሞ ከወገብ በታች ያለውን የመከላከል መዋቅር በሚያስደንቅ ወቅታዊ ብቃት እንደሚገኝ ጠቋሚ ነው። ቡድኑ ባሳለፍነው ሳምንት ጠንከር ያለ ፍልሚያ በተደርገበት መርሐ-ግብር ድል አድርጎ ወደ ነገው ጨዋታ መቅረቡ እንዲሁም ጨዋታው ለቡድኑ ካለው ዋጋ አንፃር ቅድሚያ የማሸነፍ ግምት እንዲሰጠው ያደርጋል።

በወልዋሎ በኩል ጉዳት ላይ የሰነበቱት ቡልቻ ሹራ፣ ናትናኤል ዘለቀ፣ ሳሙኤል ዮሐንስ እና ሳምሶን ጥላሁን ነገም በጉዳት በጨዋታው አይሳተፉም፤ ሰመረ ኪዳነ ማርያምም ሌላው በጉዳት ምክንያት ቡድኑን የማያገለግል ተጫዋች ነው። ዳዋ ሆቴሳም በቤተሰብ ጉዳይ ከቡድኑ ጋር አይገኝም።
በኢትዮጵያ ቡና በኩል አጥቂው አንተነህ ተፈራ፤ በትከሻ ጉዳት ጠንካራ ጉዳት የገጠመው እያሱ ፈጠነና አሁንም ከጉዳት ማገገም ያልቻለው መላኩ አየለ በነገው ጨዋታ ላይ አሁንም የማይኖሩ ይሆናል።

የተሰረዘውን የ2012 ውድድር ዓመት ጨዋታ ሳይጨምር በሊጉ 5 ጊዜያት የተገናኙት ቡድኖቹ ኢትዮጵያ ቡና 3 በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል።  አንድ ጨዋታ ወልዋሎ ድል ሲያደርግ አንድ ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል። ቡና 4 ሲያስቆጥር ወልዋሎ 2 አስቆጥሯል።