ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ወላይታ ድቻ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ወላይታ ድቻ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ


ከስጋት ቀጠናው ለመራቅ ከድል ጋር መታረቅ የሚጠበቅበት ኤሌክትሪክ ከ ጦና ንቦቹ ጋር የሚፋለሙበት ጨዋታ የዕለቱ ሦስተኛ መርሐግብር ነው።

በአርባ ሁለት ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ወላይታ ድቻዎች ከሦስት ጨዋታዎች በኋላ ድል አድርገው በሰንጠረዡ አካፋይ ላይ ለመደላደል ወደ ሜዳ ይገባሉ።

በሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች ከተቋጨው የሀዋሳ ቆይታቸው በኋላ በመጨረሻው መርሐግብር ከመቻል ጋር ነጥብ በመጋራት የአዳማ ቆይታቸውን የጀመሩት የጦና ንቦቹ በተለመደው ቀጥተኛ ኳስ መሰረት ባደረገ አጨዋወት በቀረቡበት ጨዋታ ላይ ዘለግ ላሉ ደቂቃዎች መምራት ቢችሉም በጨዋታው መገባደጃ ደቂቃ ላይ ባስተናገዱት ግብ ነጥብ ተጋርተው መውጣታቸውን ተከትሎ ደረጃቸውን የሚያሻሽሉበትን ዕድል አባክነዋል። ቡድኑ በዕለቱ በኳስ ቁጥጥርም ሆነ የግብ ዕድሎች በመፍጠር ረገድ ብልጫ ቢወሰድበትም ከተጋጣሚው ጥንካሬ አንፃር ያሳየው እንቅስቃሴ እንዲሁም ከተከታታይ ሽንፈቶች ማገገሙ በአወንታ የሚጠቀስለት ነጥብ ነው፤ ሆኖም ከሦስት የጨዋታ ሳምንታት በኋላ ወደ ድል መንገድ ለመመለስ የማጥቃት አጨዋወቱን ጥራት ማሳደግ ይኖርበታል።

በሰላሣ አራት ነጥቦች 14ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ከስጋት ቀጠናው ለመራቅ ለሳምንታት ከናፈቃቸው ድል ጋር መታረቅ ይኖርባቸዋል።

ድል ካደረጉ አምስት የጨዋታ ሳምንታት ያስቆጠሩት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ከሦስት ተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች አገግመው በመደዳ ነጥብ መጋራት ቢችሉም ተከታዮቻቸው መቐለ 70 እንደርታ እና አዳማ ከተማ ድል ማድረጋቸውን ተከትሎ ይበልጥ ስጋት ላይ ወድቀዋል። ከውድድር ዓመቱ አጋማሽ በኋላ በሁለት ጨዋታዎች ብቻ ድል ማድረግ የቻሉት ኤሌክትሪኮች በሁለተኛው ዙር በብዙ መለኪያዎች የወረደ ብቃት አሳይተዋል። በተለይም በውድድር ዓመቱ የቡድኑ ዋነኛ ደካማ ጎን ሆኖ የዘለቀው እና ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ውስጥ በሦስቱ ኳስና መረብ ማገናኘት ያልቻለው የማጥቃት ክፍሉ በቡድኑ ውጤት ላይ አሉታዊ አስተዋፅዖ አድርጓል። ቡድኑ ዝቅተኛ የግብ መጠን በማስቆጠር በጣምራ ከሚመሩት ወልዋሎ እና ስሑል ሽረ፣ እንዲሁም ሃያ ሁለት ግቦችን ካስቆጠረው መቐለ በመቀጠል ዝቅተኛ የግብ መጠን ያስቆጠረ መሆኑም የፊት መስመሩን ድክመት ማሳያ ነው። ይህንን ተከትሎ የቡድኑ የሊጉ ቆይታ በሚወስኑ ቀሪ ወሳኝ መርሐ-ግብሮች የማጥቃት አጨዋወቱን ማሻሻል ከቡድኑ ይጠበቃል።

በወላይታ ድቻ በኩል ካርሎስ ዳምጠው እና ያሬድ ደርዛ በቅጣት ብስራት በቀለ እና ግብጠባቂው ቢኒያም ገነቱ በጉዳት በነገው ጨዋታ ማይኖሩ ሲሆን በመጨረሻው ጨዋታ ያልነበረው ፍፁም ግርማን ጨምሮ ሌሎቹ የቡድኑ አባላት ግን ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው። በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል ከተከላካዩ አብዱላሂ አላዩ በስተቀር የተሟላ ስብስባቸውን ይዘው የሚቀርቡ ይሆናል።

ቡድኖቹ ከዚህ ቀደም 13 ጊዜ ተገናኝተዋል፤ ሁለቱም በእኩሌታ 3 ጨዋታዎች ሲያሸንፉ በ 7 አጋጣሚዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ወላይታ ድቻ 11 ኢትዮ ኤሌክትሪክ ደግሞ 10 ግቦች አስቆጥረዋል።