አዞዎቹ የሰንጠረዡን አካፋይ ለመሻገር ቡናማዎቹ ደግሞ ጨርሶ ያልጠፋውን የዋንጫ ዕድላቸው ለማለምለም የሚፋለሙበት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
ከተከታታይ አራት ሽንፈቶች በኋላ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች አራት ነጥቦች አስመዝግበው መጠነኛ እፎይታ ያገኙት አዞዎቹ ከስምንት የጨዋታ ሳምንታት በኋላ ያስመዘገቡት ድል ማስቀጠል ቢያንስ በሰንጠረዡ አጋማሽ እንዲረጉ ስለሚረዳቸው መርሐ-ግብሩ ወሳኝ ነው።
በሰላሣ ዘጠኝ ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት አርባ ምንጭ ከተማዎች በስምንት የጨዋታ ሳምንታት ማግኘት ከሚገባቸው ሀያ አራት ነጥቦች ሦስቱን ብቻ በማሳካት ደካማ ውጤቶች ካስመዘገቡ በኋላ ከሰንጠረዡ የላይኛው ክፍል ተንሸራተው ወደ ስጋት ቀጠናው ቀርበው የነበረ ቢሆንም በመጨረሻው ጨዋታ ባህርዳር ከተማ ላይ ባስመዘገቡት እጅግ ወሳኝ ድል ከስጋት ቀጠናው ፈቀቅ እንዲሉ አስችሏቸዋል።
ከመጨረሻው ጨዋታ በፊት በተካሄዱ ሰባት ጨዋታዎች ላይ ሁለት ጊዜ ብቻ ኳስ እና መረብን ያገናኙት አርባምንጮች የጣና ሞገዶቹን በገጠሙበት መርሐ-ግብር ግን ከወትሮ የተሻለ የማጥቃት ጥንካሬ ነበራቸው፤ ቡድኑ በዕለቱ በሰባት መርሐ-ግብሮች ያስቆጠራቸው ድምር ግቦች በአንድ ጨዋታ ከማስቆጠሩም በተጨማሪ ከሌላው ጊዜ አንፃር ሲታይ የመጨረሻ የግብ ዕድሎችን የፈጠረባቸው አጋጣሚዎችም በርካታ ነበሩ። ይህንን ተከትሎ በፊት መስመሩ የታየው መሻሻል እንዲሁም በአምስት ጨዋታዎች ሰባት ግቦች ካስተናገደ በኋላ መረቡን አስከብሮ የወጣው የተከላካይ መስመር ጥንካሬ ማስቀጠል አሰልጣኝ በረከት ደሙ የሚጠብቃቸው የቤት ስራ ነው።
በሀምሳ አምስት ነጥቦች 2ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኢትዮጵያ ቡናዎች ጨርሶ ያልጠፋው የዋንጫ ተስፋቸውን ማለምለም የሚችል ድል ፍለጋ አዞዎቹን ይገጥማሉ።
ከተከታታይ አምስት ድሎች በኋላ ሳይጠበቁ መውረዱን ባረጋገጠው ወልዋሎ ነጥብ የጣሉት ቡናማዎቹ በነገው ዕለት ድል ማድረግ የሚችሉ ከሆነ መሪው መድን ጨዋታውን እስኪያከናውን ድረስ በጊዜያዊነት የነጥብ ልዩነቱን ወደ አምስት ማጥበብ ይችላሉ። ቡናማዎቹ ከወልዋሎ ጋር አቻ ተለያይተው ወርቃማ ነጥቦች በጣሉበት ጨዋታ እንደ ወትሮ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ መውሰድ ቢችሉም በተጋጣሚ የግብ ክልል በነበሩ ጥድፍያዎች እንዲሁም በውሳኔ አሰጣጥ ድክመቶች መነሻነት ዕድሎችን አባክነዋል። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረጉት የድሕረ ጨዋታ ቆይታ ተጫዋቾቹ የመሪውን ውጤት አይተው መግባታቸው እና የነጥብ ልዩነቱን ለማጥበብ ባደረጉት ጥረት በውስን መልኩ ስሜታዊ እንደነበሩ የጠቀሱት አሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ በዋንጫ ፉክክሩ ለመቆየት በሚያደርጉት ወሳኝ መርሐ-ግብር በመጨረሻው ጨዋታ የተስተዋሉ ጥድፍያዎች ማረም ይኖርባቸዋል።
በአርባምንጭ ከተማ በኩል በላይ ገዛኸኝ እና አሸናፊ ተገኝ በጉዳት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጭ ሲሆኑ የተከላካዩ አሸናፊ ፊዳ መሰለፍም አጠራጣሪ ነው። ኢትዮጵያ ቡናዎች ረጅም ጉዳት ላይ ከነበሩት አንተነህ ተፈራ፣ እያሱ ፈጠነ እና መላኩ አየለ በተጨማሪ ወልደአማኑኤል ጌቱ እና አማኑኤል አድማሱን በጉዳት ራምኬል ጀምስን ደግሞ በቅጣት ምክንያት የማያሰልፉ ይሆናል።
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ለ19 ጊዜያት የተገናኙ ሲሆን ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ ሰባት ሰባት ድሎች ስያሳኩ የተቀሩት አምስት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል።