ሪፖርት | በጭማሪ ደቂቃ ጎል ነብሮቹ ከመቻል ጋር ነጥብ ተጋርተዋል

ሪፖርት | በጭማሪ ደቂቃ ጎል ነብሮቹ ከመቻል ጋር ነጥብ ተጋርተዋል

ሀድያ ሆሳዕና በጭማሪ ደቂቃ ባስቆጠሯት ግብ ከመቻል ጋር 1ለ1 ተለያይተዋል።

ሀድያ ሆሳዕና ከአዳማው የ1ለ0 ሽንፈት በሦስቱ ላይ ለውጥን ሲያደርጉ ፀጋአብ ግዛውን በቃለአብ ውብሸት ፣ አብዱላሂ ሀሚሲን በብሩክ ማርቆስ ፣ ደስታ ዋሚሾን በእዮብ አለማየሁ ሲተኩ በሀዋሳ በተመሳሳይ ሽንፈት ያስተናገዱት መቻሎች በበኩላቸው የአምስት ተጫዋቾችን ለውጥ በማድረግ ሲገቡ አስቻለው ታመነ ፣ ፍሪምፓንግ ሜንሱ ፣ ፊልሞን ገብረፃዲቅ ፣ ኮሊን ኩጆ ኮፊ እና ዮሴፍ ታረቀኝን በነስረዲን ሐይሉ ፣ ዳዊት ማሞ ፣ አብዱልከሪም ወርቁ ፣ ዮሐንስ መንግስቱ እና አቤል ነጋሽ በመተካት ቀርበዋል።

ደረጃቸውን ለማሻሻል በሳምንቱ የማሳረጊያ ቀን የመጀመሪያ በሆነው መርሀ-ግብር የተገናኙት ቡድኖቹ በመጀመሪያው አጋማሽ የመጀመሪያዎቹን አስር ደቂቃዎች መጠነኛ መቀዛቀዝን ቢያሳዩንም ቀስ በቀስ በመረጡት የጨዋታ መንገድ ጥራት አይታከልበት እንጂ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ መድረስ ግን ችለዋል። እዮብ አለማየሁ ከሳጥን ውጪ ባደረጋት ጠጣር ሙከራ ግብ ጠባቂው ውብሸት ጭላሎ በያዘበት አጋጣሚ ቀዳሚ መሆን የቻሉት ነብሮቹ ሦስቱን ፈጣን የፊት አጥቂዎች ትኩረት ያደረገ ረጃጅም ኳስን በመጠቀም በጥልቅ እንቅስቃሴ ለመጫወት ጥረት ሲያደርጡ የኳስ ቁጥጥር ብልጫውን ወስደው በንክኪ ሦስተኛው ሜዳ ላይ መቻሎች በመድረስ ግን በይበልጥ የተሻሉ ነበሩ።

በ15ኛው ደቂቃ ሽመልስ በቀለ ከቀኝ በኩል ከቅጣት ያሻማውን በረከት ደስታ በግንባር ገጭቶ ለጥቂት ዒላማዋን መጠበቅ ባልቻለች ሙከራን ማድረግ የጀመሩት መቻሎች ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ የተሻለውን ዕድል አምክነዋል። አብዱልከሪም ወርቁ ከጥሩ የእግር ስራ በኋላ ወደ ቀኝ ሳጥኑ የሰጠውን በረከት ደስታ መቶ ስንታየሁ ታምራት ያመካናት የአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቡድን የሰነዘራት ከፍ ያለች ሙከራቸውም ነበረች። ጥሩ ፉክክርን ብናይበትም በጠሩ የግብ ዕድሎች መድመቅ ያልቻለው ጨዋታ ከቆሙ ኳሶች በመቻል በኩል ሽመልስ አከታትሎ አሻምቶ መጠቀም ያልቻሉበት እንዲሁም በሀድያ ሆሳዕና ደግሞ 29ኛው ደቂቃ በመልሶ ማጥቃት በግራ ሳጥን ውስጥ ሠመረ ያገኘውን ኳስ ሞክሮ በቀላሉ በውብሸት የተያዘበት በአጋማሹ የታዩ ውስን ጥራት አልባ ዕድሎች ሆነዋል።

መቻሎች ዮሐንስ መንግስቱን በፊሊሞን ገብረፃዲቅ ተክተው በተመለሱበት ሁለተኛው አጋማሽ ከመስመር በሚጣሉ ኳሶች ሀድያ ሆሳዕና ጥሩ አጀማመር የነበራቸው ቢመስልም የመጨረሻው ሜዳ ላይ ኮስታራ ባለመሆናቸው እንቅስቃሴያቸውን እያሳደጉ በመጡት መቻሎች በብዙ ረገድ ለመበለጥ ተገደዋል። በ60ኛው ደቂቃ የሀድያው የግብ ዘብ ስንታየሁ ታምራት ከሔኖክ አርፊጮ ወደ ኋላ የደረሰውን ኳስ በአግባቡ መቆጣጠሩ አቅቶት አቤል ነጥቆት ሽመልስ ተቀብሎ አቤል የመጨረሻዋን ሙከራ አድርጎ አምክኗታል።

63ኛው ደቂቃ እዮብ አለማየሁ እና ተመስገን ብርሀኑ ሁለት ጊዜ ሙከራን አድርገው ውብሸት ጭላሎ ካመከነው በኋላ በተጋጣሚያቸው ጫና ያደረባቸው ነብሮቹ 64ኛው ደቂቃ ሽመልስ በቀለ ሳጥን ውስጥ በቀኝ ክፍል ከአብዱልከሪም ያገኘውን ኳስ ሞክሮ ግብ ጠባቂው ስንታየሁ ታምራት ካዳናት ከሁለት ደቂቃዎች መልስ በጥሩ ቅብብል አብዱልከሪም ለበረከት ሰጥቶት ተቀይሮ የገባው ፊልሞን ገብረፃዲቅ ገብረፃዲቅ ከበረከት የተቀበለውን ኳስ ከሳጥን በማስቆጠር መቻልን መሪ አድርጓል።

ጎል ካስቆጠሩ በኋላ በሀድያ ሆሳዕና የሽግግር አጨዋወት ጫና ያደረባቸው መቻሎች ግልፅ ጎል አስቆጥረው በረዳት ዳኛዋ ወጋየሁ ዘውዴ ከጨዋታ ውጪ ተብላ ከተሻረች ጭማሪው ደቂቃ 90+3 ላይ ናትናኤል ሞገስ ከማዕዘን አሻምቶ ብሩክ ማርቆስ በግንባር ገጭቶ አግዳሚ ብረቱን ነክታ ኳሷ ስትመለስ ግብ ጠባቂው ውብሸት ጭላሎ በጭንቅላቱ ነክቷት መረቡ ላይ አርፋ በግብ ጠባቂው ጎሏም ከተመዘገበች በኋላ በመጨረሻም 1ለ1 በሆነ ውጤት ፍፃሜውን ጨዋታው አግኝቷል።


ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የመቻሉ አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ብዙ የጎል ዕድሎችን አግኝተው መረጋጋት ስላልነበር መጠቀም እንዳልቻሉ ውጤቱንም ለመቀበል እንደሚገደዱ ገልፀው ያለፉ ውጤቶች በቡድኑ ላይ ጫናን ማምጣታቸውን በመጠቆም ስለሚሳቱ ኳሶች በአንፃሩ ጎል ጋር የማድረስ ስራን አሰልጣኝ ይሰራል ማግባት ደግሞ የተጫዋች እንደሆነ ዓመቱ በአጠቃላይ ለቡድናቸው ጥሩ እንዳልነበር ተናግረዋል። የሀድያ ሆሳዕናው አሰልጣኝ ግርማ ታደሠ በበኩላቸው ጎል ከማስቆጠራቸው በፊት ከጨዋታ ውጪ ተብላ የተሻረችባቸው ጎል ትክክል አለመሆኑን በሷም የተነሳ የአቻነት ጎል ሲቆጠር ደስታቸው ከፍ ያለ እንደነበር ከተናገሩ በኋላ ተጫዋቾቻቸው የመጨረሻው የሜዳ ክፍል ላይ የሚገኙ ዕድሎችን እንደሚያባክኑ ይሄንንም ለማስተካከል ሰፊ ጊዜ ያስፈልጋል ካሉ በኋላ በቡድኑ ውስጥ ያሉ ችግሮች በሁለተኛው ዙር ጥሩ ውጤት መያዝ እንዳይችሉ በማድረጉ ደጋፊውን ይቅርታ እንደሚጠይቁ በንግግራቸው ጠቁመዋል።