ስድስት ጎሎችን ባስመለከተን መርሀ-ግብር አዳማ ከተማ 4ለ2 በሆነ ውጤት ስሑል ሽረን በመርታት በሜዳው ተከታታይ አራተኛ ድሉን በማስመዝገብ ከወራጅ ቀጠናው ማንሰራራቱን ቀጥሏል።
በሀዋሳ የ5ለ1 ሽንፈት ስሑል ሽረዎች የአምስት ተጫዋቾችን ለውጥ ሲያደርጉ ሞይስ ፓዎቴ ፣ አሰጋኸኝ ጴጥሮስ ፣ ሙሉአለም መስፍን ፣ አብዲ ዋበላ ፣ ኤልያስ አህመድ እና ፋሲል አስማማውን በማሳረፍ ዋልታ አንድዬ ፣ ሠለሞን ገብረክርስቶስ ፣ ነፃነት ገብረመድህን ፣ ብሩክ ሀዱሽ ፣ አላዛር ሽመልስ እና ሔኖክ ተወልደ ተተክተው ሲገቡ ባህርዳር ከተማን 2ለ0 የረቱት አዳማ ከተማዎች ግን ምንም ለውጥ ሳያደርጉ ቀርበዋል።
የሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን ሁለተኛ ጨዋታ ከአሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊት ጋር የተለያዩት ስሑል ሽረዎች መውረዳቸውን ቢረጋገጥም ለክብር ፣ አዳማዎች በበኩላቸው በሊጉ የመቆየት ተስፋቸውን ለማለምለም ያደረጉት የምሽቱ መርሀ-ግብር በመጀመሪያው ሀያ ደቂቃዎች በሁለቱም መስመር በኩል በጥልቅ እንቅስቃሴ ፍፁማዊ ብልጫን ያሳየው አዳማዎች በተከታታይ ሙከራን የሰነዘሩበት ነበር።
5ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር ቻላቸው መሬት ለመሬት የሰጠውን ነቢል ኑሪ ሞክሮ ኳሷ ዒላማዋን ሳትጠብቅ በላይኛው አግዳሚ በኩል ከወጣች ከስምንት ደቂቃዎች መልስ ጫናቸውን ይበልጥ በማሳደግ ከቀኝ ቻላቸው መንበሩ ወደ ውስጥ ያሻገረውን ኳስ የሽረው ተከላካይ ሠለሞን ገብረክርስቶስ በራሱ ላይ አስቆጥሯታል።
በ20ኛው ደቂቃ ነቢል ከቀኝ ያስጀመረውን ኳስ ቢኒያም ከጎኑ ለነበረው ሙሴ ኪሮስ ሰጥቶት አማካዩ ወደ ጎል መቶ በተከላካዮች ተጨርፋ አድናን ረሻድ ያገኘውን ኳስ ወደ ጎልነት ለውጦ የቡድኑን የጎል መጠን አሳድጎታል።
መሪ የሆኑባቸውን ጎሎችን ካገኙ በኋላ መጠነኛ መቀዛቀዝን ውስጥ የገቡት አዳማዎች ተጋጣሚያቸው በመስመር በሚሻገሩ ኳሶች ለጥቂት ደቂቃ በወሰደባቸው ብልጫ ጎል አስናግደዋል። በ29ኛው ደቂቃ ሔኖክ ተወልደ ከግራ ወደ ውስጥ ያሻማውን ኳስ የግብ ዘቡ ናትናኤል ተፈራ ዝንጉነት ታክሎ ብርሀኑ አዳሙ በግንባር ገጭቶ ጨዋታውን 2ለ1 ማድረግ ችሏል። በቀጣዮቹ ደቂቃዎች አላዛር ሽመልስ ከርቀት የመታትን ኳስ ናትናኤል ተፈራ ካመከነው በኋላ እየወረዱ የመጡት ሽረዎች በተቃራኒው ጥቃቶችን ማስተናገድ ደግሞ ጀምረዋል።
39ኛው ደቂቃ ነቢል ኑሪ ሙከራ አድርጎ በግብ ዘቡ ዋልታ አንድዬ ከተመለሠ ሦስት ደቂቃዎች እንደተቆጠረ ከአላዛር ሽመልስ የተነጠቀ ኳስን አድናን ረሻድ ወደ ቀኝ ሳጥን ለቢኒያም ዐይተን ሰቶ ወጣቱ አጥቂም በጥሩ አጨራረስ ከመረብ አዋህዷታል።
ከጎሏም በኋላ በቻላቸው መንበሩ ሌላ አጋጣሚን ቢያገኙም በክፍሎም ብርሀነ ድንቅነት ዕገዛ ግብ መሆን ሳትችል ጨዋታው ተጋምሷል።
ስሑል ሽረዎች የተጫዋቾችን ቅያሪ በማድረግ የተመለሱበት ሁለተኛው አጋማሽ በመፈራረቅ ብልጫውን ለመውሰድ የተደረገ እንቅስቃሴዎችን ያስተዋልንበት ነበር። አዳማ ከተማ ነቢል ፣ ሙሴ እና ቢኒያምን በመጠቀም በድግግሞሽ የመጨረሻው ሜዳ ላይ በመድረስ የኳስ ቁጥጥር ብልጫውን መያዝ ቢችሉም የተጋጣሚያቸውን ፈጣን ሽግግር በቀላሉ መቋቋም ግን በተቃራኒው ከብዷቸው ለጥቂትደቂቃዎች አስተውለናል። 52ኛው ደቂቃ ላይ ሳጥኑ ጠርዝ ላይ ስሑል ሽረዎች ያገኙት የቅጣት ምት አላዛር ሽመልስ በግሩም ሁኔታ የናትናኤል ተፈራ መረብ ላይ በማሳረፍ የጨዋታውን ግለት ከፍ ያደረገች ግብ አድርጓታል።
የፉክክር መንፈሱ እያደገ ቶሎ ቶሎ የመጨረሻዎቹ ሜዳዎች ላይ በሚስተዋሉ እንቅስቃሴዎች እየጎመራ የቀጠለው ጨዋታ አዳማ 60ኛው ደቂቃ ቢኒያም ከማዕዘን አሻምቶ ሙሴ ኪሮስ በሴንቲ ሜትር ልዩነት በግንባር በቀላሉ ያመከነው ከአምስት ደቂቃ በኋላ ደግሞ ነቢል ከቅጣት ያሻገረለትን ኳስ ቢኒያም በግንባር ገጭቶ የግቡ አግዳሚ ብረት የመለሰበት ሙሴ በሌላ አጋጣሚ በግብ ዘቡ ዋልታ ተመልሶበታል። 77ኛው ደቂቃ ላይ ብርሀኑ አዳሙ ለስሑል ስረ ጥሩ ዕድልን ፈጥሮ ሃይለሚካኤል ካስጣለው አጋጣሚ በኋላ ቀስ በቀስ በአዳማ የተበለጠው ቡድኑ 85ኛው ደቂቃ ነቢል ኑሪ ከሙሴ ኪሮስ ያገኛት ኳስን በግራ ለተገኘው ቢኒያም አቀብሎ አጥቂውም ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ አራተኛ ጎል ሲያደርግ በሽርፍራፊ ሰከንዶች ውስጥ ሽረዎች በአወት እና ሔኖክ ካደረጓቸው ሙከራዎች መልስ 4ለ2 በሆነ የአዳማ አሸናፊነት ተቋጭቷል።
ከጨዋታው መቋጫ በኋላ አሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊትን ተክተው ጊዜያዊ አሰልጣኝ የሆኑት የቀድሞው የቡድኑ ተጫዋች መብራሀቶም ፍሰሀ በመጀመሪያው ሀያ ደቂቃዎች ውስጥ የተቆጠሩባቸው ጎሎች በቡድኑ ላይ መዘናጋትን እንደፈጠረ በመግለፅ በዛሬው ጨዋታ የተጠቀሟቸው አማካዮች አዲስ በመሆናቸው የቅንጅት ክፍተት እንደታየ ከዕረፍት መልስ ግን እንደተጠበቀው ባይሆንም በቅያሪ ተጫዋቾች የተወሰነ ለውጥ መታየቱን ነገር ግን በመጀመሪያው አጋማሽ ብዙ ነገሮችን እንደተበላሸ ጠቁመዋል። የአዳማ ከተማው አሰልጣኝ አብዲ ቡሊ በበኩላቸው ጨዋታው ውጥረት እንደነበረበት ጎል አስቆጥረው በነፃነት መጫወት ሲችሉ ያ መሆን እንዳልቻለ በመናገር ኳስን ከራስ ሜዳ ይዘው ሲወጡ ስህተቶች መታየት እንደቻሉ እና ብዙ ጎል አገባለው የሚል ጉጉት መታየቱን ነገር ግን ጨዋታውን አሸንፈው መውጣታቸው ደስ እንዳሰኛቸው ተናግረዋል።