ሪፖርት | አዳማ ከተማ ከፋሲል ከነማ ጋር ነጥብ በመጋራቱ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል

ሪፖርት | አዳማ ከተማ ከፋሲል ከነማ ጋር ነጥብ በመጋራቱ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል

በሊጉ ለመክረም እጅግ ብርቱ ፉክክር የተደረገበት እና ከዕረፍት በፊት 2ለ0 ሲመራ የነበረው አዳማ ከተማ በተቃራኒው ከዕረፍት መልስ ባስተናገዳቸው ጎሎች 2ለ2 በመለያየቱ ራሱን አደጋ ውስጥ ጥሏል።

በ34ኛ የጨዋታ ሳምንት ተጋጣሚያቸውን ቡድኖቹ ድል ሲያደርጉ ከተጠቀሙት ቋሚ አሰላለፍ ውስጥ ፋሲሎች አሚር ሙደሲርን በበረከት ግዛው ስሑል ሽረን የረቱት አዳማዎች ደግሞ ቻላቸው መንበሩን በመላኩ ኤልያስ በተመሳሳይ ለውጠው ለጨዋታው ቀርበዋል።

ቢሾፍቱ ላይ በጣለው ከባድ ዝናብ ለአስራ ስምንት ደቂቃዎች ያህል ዘግይቶ ለመጀመር የተገደደው የአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂው ሜዳ ያስተናገደው የፋሲል እና አዳማ ጨዋታ በኢንተርናሽናል ዳኛ ማኑሄ ወልደፃዲቅ እየተመራ የጀመረ ነበር። በመጀመሪያዎቹ አምስት ደቂቃዎች ለሽግግር ቅድሚያውን ሰጥተው የተሻለ አጀማመርን ያሳዩት አፄዎቹ በ3ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ቃልኪዳን ሲያሻማ አማኑኤል ገብረሚካኤል ለጥቂት በወጣችበት አጋጣሚ ሙከራን በማድረግ ቀዳሚ ቢሆኑም ከመስመር በመነሳት በጥልቀት መንቀሳቀስ የጀመሩት አዳማዎች ግን ተጋጣሚያቸው ደጋግሞ በመከላከሉ በሚሰራቸው ስህተት ጎል በማስቆጠር ቀድመዋል።

በ7ኛው ደቂቃ በሳጥኑ ጠርዝ እዮብ ማቲያስ ቢኒያም ዐይተን ላይ በሰራው ጥፋት የተገኘን የቅጣት ምት ነቢል ኑሪ እጅግ ግሩም አድርጎ በመምታት ፋሲል ገብረሚካኤል መረብ ላይ ኳሷን አሳርፏታል። 11ኛው ደቂቃ ጌታነህ ከበደ ወደ ግራ ካደላ ቦታ ከቅጣት ምት ወደ ግብ ሞክሮ ናትናኤል ተፈራ ካወጣበት ቀጣዮቹም ደቂቃዎች በተቃራኒው የኋላ ክፍላቸውን ማሻሻል ያልቻሉት አፄዎቹ ሁለተኛ ጎል ተቆጥሮባቸዋል። 23ኛው ደቂቃ በጥሩ ቅብብል በቀኝ ሳጥን ውስጥ ነቢል ኑሪ የተከላካዮችን ዝንጉነት ተመልክቶ ያቀበለውን ኳስ አድናን ረሻድ መረቡ ላይ በማሳረፍ ወደ 2ለ0 ቡድኑን አሸጋግሯል።

30ኛው ደቂቃ ላይ ቢኒያም ዐይተን ራሱ ያስጀመራትን ኳስ ከነቢል መልሶ ተቀብሎ ከግብ ዘቡ ፋሲል ጋር ተገናኝቶ ሳይጠቀምባት ከቀረ በኋላ ጨዋታው ሊገባደድ አስር ደቂቃዎች ሲቀሩ አቤል እንዳለ እና ማርቲን ኪዛን በአንዋር ሙራድ እና ቢኒያም ጌታቸው የተኩት አፄዎቹ የተሻሻለውን እንቅስቃሴ ቢያደርጉም አጋማሹ ግን በአዳማ የበላይነት ተጋምሷል።

ከዕረፍት መልስ ከጅምሩ በፈጣን ሽግግር ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረቶችን ከፍ አድርገው ያመላከቱን ፋሲሎች 51ኛው ደቂቃ ላይ ጎል ማስቆጠር ችለዋል። ፍቅሩ አለማየሁ ሳጥን ውስጥ በአንዋር ሙራድ ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠን የፍፁም ቅጣት ምት ጌታነህ ከበደ ወደ ጎልነት ለውጦ ጨዋታው 2ለ1 መሆን ችሏል። ሁለት ለምን መምራታቸው ወደ ኋላ አፈግፍገው እንዲጫወቱ ያደረጋቸው አዳማዎች በተጋጣሚያቸው ወደ ሳጥን በሚጣሉ እና በሽግግር ኳሶች በመበለጣቸው 67ኛው ደቂቃ ላይ ጌታነህ ከበደ ከረጅም ርቀት ከቅጣት ምት ወደ ሳጥን ሲያሻማ አንዋር ሙራድ በግንባር ጨርፎ ወጣቱ የግብ ዘብ ናትናኤል ተፈራ እጅግ ደካማ የሆነው የጊዜ አጠባበቅ ስህተት ታክሎበት ኳሷ መስመሩን በማለፏ ጨዋታው 2ለ2 ለመሆን ተገዷል። በቀጣዮቹ ደቂቃዎች በአዳማ በኩል ከማዕዘን በቀጥታ ነቢል አሻምቶ ፋሲል ገብረሚካኤል ካወጣት ሙከራ በኋላ በቀሩት ደቂቃዎች በሙከራዎች መድመቅ የተሳነው ጨዋታው 2ለ2 ሲጠናቀቅ ለፋሲል እፎይታ ለአዳማ ደግሞ አስጊ ውጤት ተመዝግቦበታል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የአዳማ ከተማው አሰልጣኝ አብዲ ቡሊ በመጀመሪያው አርባ አምስት የተሻሉ እንደነበሩ እና ጨዋታውን ለመጨረስ ቢያስቡም በሁለተኛው አጋማሽ ግን በነበሩ መጨናነቆች ይዘው የነበረውን ውጤች ከእጃቸው ሊያጡት እንደቻሉ በመግለፅ ለማተካከል ያደረጉት ጥረትም መሳካት እንዳልቻለ ነገር ግን በቀጣይ የመጨረሻ ጨዋታቸውን አሸንፈው በሊጉ ለመቆየት ጥረት እንደሚያደርጉ ለዛም ተስፋ እንደማይቆርጡ ጠቁመዋል። የፋሲል ከነማው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በበኩላቸው በመጀመሪያው ሀያ ደቂቃዎች ጎል ማስተናገዳቸው ላለመውረድ ከሚጫወት ቡድን የማይጠበቅ መሆኑን ገልፀው በአጋማሹም በጊዜ ያደረጉት ቅያሪ ለሁለተኛው አጋማሽ መሻሻል ግብዓት እንደነበር ጥሩ ውጤትም ይዘው ሊወጡ እንደቻሉ በመጠቆም ከተወለዱበት እና አሰልጥነው ካለፉበት አዳማ ከተማ ጋር በዚህ ጊዜ መገናኘታቸው መጥፎ መሆኑን ጨዋታው ግን ጥሩ እንደነበር ተናግረዋል።